Sunday, December 15, 2019
Home > ዜና > ከ2 ሺህ 600 በላይ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ

ከ2 ሺህ 600 በላይ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ወጣ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ2 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ አውጥቶባቸዋል።

የእጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ሀላፊዎች እና የህብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት ነው የተካሄደው።

በዚህ ስነ ስርዓት ላይም ግንባታቸው የተጠናቀቁ 2 ሺህ 6ዐ5 የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ወጥቶባቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፥ የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር ለመፍታት አስተዳደሩ ባለፉት ጊዜያት በ11 ዙሮች ከ176 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ማስተላለፉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከ132 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ግንባታዎች በመገባደድ ላይ በመሆናቸው በቅርቡ ለእድለኛች ለማስረከብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገላጸዋል።

በእጣ ማውጣት ስነስረአቱ የ1997 ዓ.ም ነባር ተመዝጋቢ ሆነው ምዝገባቸውን በ2005 ዓ.ም ያደሱ የባለ 3 መኝታ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ በዚህ ዙር የቤት ባለቤት ሆነዋል።

በዛሬው እለት ባለእድል የሆኑ የከተማ ነዋሪዎችም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የቁልፍ ርክክብ የሚደረግላቸውም በስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ተጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞቹ ለቤቱ የሚከፍሉት አጠቃላይ ዋጋም በ11ኛው ዙር ለባለ እድለኞች ከተላለፈበት ዋጋ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ተገልጿል።

FBC

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.