Wednesday, April 8, 2020
Home > ዜና > “ከኢትዮጵያዊነት አንሸሽም” ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ

“ከኢትዮጵያዊነት አንሸሽም” ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ

“ከኢትዮጵያዊነት አንሸሽም”… ዶክተር ደሳለኝ!

በዘውድአለም ታደሠ

ቤቲ ኤል ቲቪ ላይ ከአብኑ መሪ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ጋር ውይይት አድርጋ ብዙ ሰዎች የተለያየ ነገር ሲሉ ተመልክቼ ሙሉ ቃለመጠይቁን ተመለከትሁ።

እውነት ለመናገር የቤቲ ጥያቄዎችና ግብረመልሶች ያልበሰሉና ከጋዜጠኝነት ሚና ወጣ ያሉ (ፈራጅነት የታየባቸው) ነበሩ። ምናልባት የጋዜጠኝነት ትምህርት ስላልተማረች ዘርፍና ድርሻዋን ካለማወቅ ሊሆን ይችላል።

የአማራ ገበሬ አልተጠቀመም ስትባል የኦሮሞ ገበሬስ መች ተጠቀመ? ብላ ትርጉም የሌለው ሙግት ውስጥ ትገባለች። የአማራ ገበሬን ችግር ለማንሳት የግድ የኦሮሞ ገበሬ መጠቀም አለበት እንዴ? ዶክተሩ የአማራ ድርጅት ሊቀመንበር ስለሆነ ሊጠየቅ የሚገባው ስለሚታገልለት ህዝብ ብቻ ነው። (እዚህ ጋር ዶክተሩም በጋዜጠኛዋ የተሳሳተ ጥያቄ ተመርቶ የአማራና ኦሮሞ ገበሬን ለማነፃፀር መሞከሩ ተገቢ አልነበረም)

ሌላው በአብን አመራሮች በተለያየ ግዜ የተጠቀሰውን አወዛጋቢ ገለፃ እያመጣች “ከሌላው ህዝብ ጋር ያጋጫል” እያለች ደጋግማ ስትናገር ነበር።

ሲጀምር አንድ የአብን አመራር የተናገረው ነገር ግለሰቡን ቢበዛም ድርጅቱን ሊያስጠይቅ ይችላል እንጂ በሚሊየን የሚቆጠር ህዝብ ተስማምቶ የተናገረው ይመስል ከሌላ ህዝብ ጋር የሚያጋጭበት ምንም ምክኒያት የለም። ለምሳሌ “ኢትዮጵያ ፈጣሪዋን አማራን ማክበር አለባት” ለተባለው ሃሳብ ዶክተሩ ፈጣሪ ሲባል እግዜር ነን ማለት እንዳልሆነ ፈጣሪን “ከመስራችነት” ጋር አያይዞ ሲመልስላትና ሌላውም ህዝብ አብሮ ሐገሩን እንደመሰረተና (እንደፈጠረ)ና ቃሉን ከአውዱ ውጪ (out of context) መተርጎም ተገቢ እንዳልሆነ ሲያስረዳት መላልሳ “ተንኳሽ ነው፣ ያጋጫል” እያለች መድረቋ አላስፈላጊ ነው።

ሌላው በአማራው ላይ ስለደረሰው ፍሬም የተደረገ ዘር ማጥፋት (systematic genocide) ሲያወራት ስለወሊድ መቆጣጠሪያ ማውራቷ የምትጠይቀውን እንጂ የሚያወራትን ለመረዳት እንደተቸገረች ያሳያል።በተረፈ ልጅቱ ወጣትና አማተር ጋዜጠኛ እንደመሆኗ ራሷን በንባብና በልምድ ካዳበረች ተስፋ ያላት ልጅ ነች። ግልፅነቷ ደስ ይላል።

ዶክተር ደሳለኝ ላይ ያየሁት እርጋታና ቀጥተኛነት የሚደንቅ ነው። ብልጣብልጥ ሆኖ ሞጋች ጥያቄዎችን በሲስተም ለማለፍ አይሞክርም። ስለኢትዮጵያዊነት የተናገራቸው እያንዳንዱ ቃላት ይማርካሉ!

አማራው በብሔር የተደራጀው ተገዶ ነው። ሁሉም በብሔር እየተደራጀ አማራውን “በብሔር አትደራጅ” ማለት ሚዛናዊ ካለመሆኑም በላይ ህዝቡን ያለተወካይ ማስቀረት ነው። ባለው ሃሳብም እስማማለሁ። ለዚህ ነው አብን መመስረቱን ስሰማ ድጋፌን የገለፅኩት። ወደፊትም ትልቋ ሐገራችንን ያማከለና ዶክተሩ እንደገለፀው በሁሉም አማራ ደም ውስጥ የምትዘዋወረውን “ኢትዮጵያን” ታሳቢ ያደረገ አቋም እስካራመዱ ድረስ እነዚህን ትንታግ ወጣቶች ሲያጠፉ እየወቀሱ፣ ጥሩ ሲሰሩ እየተመሰገኑ፣ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ባይ ነኝ።

በቀለ ገርባ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ የአማርኛ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ኢንተርቪው “እኛ ሰብአዊ ፍጡሮች ነን። ወርደን በብሔር የተደራጀነው ተገደን ነው። ወደፊት ዴሞክራሲያዊ መንግስት ቢመሰረት የኛ መኖር አስፈላጊ ላይሆን ይችላል” ብለው ነበር።

በብሔር መደራጀት ግዜ ያመጣው እዳ ነው። እኔ ኢትዮጵያዊና ከብሔርተኝነት ዘር ሳይሆን ሃሳብ ያሰባሰባቸው ግለሰቦች የመሰረቱት ፓርቲ ቢኖር ደስታዬ ነው። ነገር ግን እንደአንዳንድ የአፍሪካ ሐገራት በብሔር ወይም በሃይማኖት መደራጀት በህግ ተከልክሎ በብሔር ላይ የተደራጁ ሁሉም ፓርቲዎች እስካልፈረሱ ድረስ አማራን ለሚያህል ሰፊ ህዝብ ከብአዴን ውጪ አማራጭ አይኑርህ ብሎ መደምደም ፍርደገምድልነት ነው። በእርግጠኝነት በዘርና በጎጥ ተደራጅቶ መታገል በህግ ቢታገድ የመጀመሪያው ደጋፊ አማራው ነው።

ዶክተሩ «አማራ ከኢትዮጵያዊነት አይሸሽም። ሁሉም ከኢትዮጵያዊነት ቢሸሽ እንኳ የመጨረሻ የሚሆነው አማራ ነው!» ብለው የተናገሩት የአማራውን ነፍስያ የሚገልፅ ወርቃማ ቃል ነው! እላለሁ!X

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.