Wednesday, April 1, 2020
Home > ዜና > የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፖ) ሙሉ የአቋም ምግለጫ አወጣ!

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፖ) ሙሉ የአቋም ምግለጫ አወጣ!

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)

12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ሙሉ የአቋም መግለጫ!

=============================

ድርጅታችን የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)የ38ኛ ዓመት የምስረታ ዋዜማው ላይ ሆኖ 12ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ የ12ኛው ድርጅታዊ ጉባዔያችን በክልላችንም ሆነ በአገራችን አጋጥሞ የነበረውን የህልውና ስጋትና አደጋለመቀልበስናለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠል አስፈላጊ በሆነበትእጅግ ወሳኝና ታሪካዊ ጊዜ“የለውጡ ቀጣይነት፤ ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት”በሚል መሪ ቃል በክልላችን ርዕሰ ከተማ በውቢቷ ባህርዳር ከመስከረም 17-22 ቀን 2011 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ ቀናት አካሂደን በስኬትና በድል አጠናቀናል፡፡

መላው የድርጅታችን አባላት፣ ምልአተ ህዝቡና የትግል አጋሮቻችን በ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤያችን አዴፓ ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ በመውጣት የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችሉት ውሳኔዎችን አስተላልፎና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እንደሚወጣ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳደር በአንክሮትና በአጽንኦት ሲጠብቁት እንደነበር እኛ የዚሁ ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች በውል የተገነዘብነው ጉዳይ ነበር፡፡

በድርጅታችን አዴፓ 12ኛውታሪካዊጉባዔ በድምፅና ያለድምፅ ከተወከሉ ጉባዔተኞች በተጨማሪ በክልላችን የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የፖለቲካ ተንታኞችና አክቲቪስቶች፤ የቀድሞ ታጋዮችና የታጋይ ቤተሰቦች፤ ምሁራን፤ ባለሃብቶች፤ አትሌቶች፤ አርቲስቶች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ወኪሎችና የሚዲያ አካላት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የታደሙበትና ይሁንታ የሰጡት ታሪካዊ ጉባዔም ነበር፡፡

እኛ የአዴፓ 12ኛው ታሪካዊ ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የ11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔያችን በአቅጣጫ ያስቀመጣቸውን ጉዳዮችና የምንገኝበትን የለውጥ መድረክ መነሻ በማድረግ በተዘጋጁ የጉባዔ ሪፖርትናበድርጅታችን የኦዲት ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት፤ በድርጅታችን ህገ-ደንብ ማሻሻያ ነጥቦችና የአመራር ምርጫ አጀንዳዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ አደራና ኃላፊነት ይዘን ሃሳባችን በነጻነት በማራመድና ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል በማድረግ ድርጅታችንህዝቡ ከሚጠብቀው የአመራር ቁመና ላይ ማድረስ የሚያስችሉት ታሪካዊ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የተላለፉበት ስኬታማ ጉባኤ አካሂደናል፡፡

ድርጅታችን አዴፓባለፉት የትግልና የድል አመታት አንግቦ የተነሳውን ህዝባዊ አላማ ለማሳካት በየወቅቱ ያጋጠሙትን ችግሮችና ፈተናዎች በጽናት ታግሎ በማለፍ በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በክልላችን ብሎም በአገራችን ታሪክ ያልነበሩ ሰፋፊ የማህበራዊ ልማቶችን በማከናወን እንዲሁም መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ከተገኙት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ባሻገር የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግና የከተማውን ህዝብ ኑሮ በማሻሻል ተጨባጭ የልማት ውጤቶችን ያስመዘገበ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይሁንና እነኝህና ሌሎች የድርጅታችን ስኬቶች አሁን ለደረስንበት የትግል ምዕራፍና ከፊታችን ለሚጠብቀን ወሳኝ ህዝባዊ ተልዕኮ እርሾና ብርታት የሚሆኑን እንጂ በታሪክ ተኩራርተን እንድንኖር የማያደርጉን መሆኑን የ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች በአጽንኦት ተመልክተነዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ የተመዘገቡ ለውጦች እንደተጠበቁ ሆነው አሁንም የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮች፤የዴሞክራሲ እጦት፤ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች፤ ድህነት፣ ስራአጥነት፣የማህበራዊና የመሰረተ ልማት ተደራሽነትና ጥራት ችግሮች እና የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ባለመፈታታቸው ምክንያት በህዝባችን ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ወደ ግጭት በመግባታችን ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡ ችግሩንም ለመፍታት የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ ውስጥ ገብተን አሁን ከምንገኝበት የለውጥ ጉዞ ላይ ደርሰናል፡፡

ስለሆነም እኛ የአዴፓ የ12ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ተሳታፊዎች አሁን የደረስንበት ውስብስብ የትግል መድረክ እንቅልፍ የሚነሱ ችግሮችና ፈተናዎች ያሉበት እና ህዝባዊ ወገንተኝነትንና የአላማ ጽናትን ተላብሰን የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ በማስቀጠል ለቀጣይ ድል በቁርጠኝነት ተግተን በመስራት ያስቀየምነውን ህዝብ በመካስ እጅ ለእጅ ተያይዘን የልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ ስራችንን ለማስቀጠል ስምምነት ላይ በመድረስ ይህን ባለ7ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

1. በዚህ ታሪካዊ ጉባዔያችን አሁን የምንገኝበትን ክልላዊና አገራዊ ለውጥ ምንነት፤ በተገኙ ውጤቶች፤ እያጋጠሙ ስላሉ ተግዳሮቶችና ለውጡን ለአማራ ህዝብና ለአገራዊ አንድነታችን ጥቅም ስለምናስቀጥልበት ሁኔታ በዝርዝር ገምግመናል፡፡ ለውጡም ህዝባዊ፣ ኢህአዴጋዊና ህገ-መንግስታዊ መሆኑን፤ለአማራ ህዝብ መሰረታዊ አጀንዳዎች ምላሽ ማግኘትና አገራዊ አንድነታችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ተገንዝበናል፡፡

በመሆኑም ድርጅታችን አዴፓ የተጀመረውን ክልላዊና አገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ የሚደረጉ ሙከራዎችን፤ የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑና ለውጡን አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም ድርጊቶች፤ አሁንም በለውጥ ውስጥ ሆነን በአገራችን እያጋጠሙ ያሉትን የዜጎች ሞትናመፈናቀል እንዲሁም ማናቸውም የስርዓት አልበኝነት ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ፤ ድርጅታችን አዴፓ የለውጥ ውጤት የሆነው ነፃነትና ስርዓት አልበኝነት በፍፁም አብረው የማይሄዱ በመሆናቸው የህግ የበላይነት ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይሆንም፡፡ ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ማናቸውንም ማሻሻያዎች ጭምር ተግባራዊ በማድረግ ለውጡን የማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን!!

2. የአማራ ህዝብ ከሌሎች የአገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ነጻነትና ሉአላዊነት ተከብሮ እንዲቆይ እንዲሁም የጸረ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ ስርአት እንዲወገድ በጽናት የታገለና መስዋእትነት የከፈለ ባለታሪክ ህዝብ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ለወንድምና እህት ህዝቦች ከፍተኛ ክብር የሚሰጥና እንደ ራሱ አካል የሚመለከት፣ እንግዳ ተቀባይና ያለውን አካፍሎ የሚያበላ እሴቶች ያሉት ታላቅ ህዝብ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ተዋህዶና ተዛምዶ የመኖር ዕፁብ ድንቅ እሴት ያለው ህዝብ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ እውነተኛ ገጽታ ይህ ሆኖ እያለ በጥርጣሬ እንዲታይ የሚያደርግ የተዛባ የታሪክ ትርክትና የአስተምህሮ ስራ በሰፊው ሲሰራበት የቆየ መሆኑንና ይህ ጉዳይ ከአማራ ህዝብ አልፎ ኢትዮጵያዊነትን ምን ያህል እየጎዳው እንደሆነ በጥልቀት ገምግመናል፡፡ ስለሆነም በአገራችን እየተገነባ የሚገኘው ህገ-መንግስታዊ ፌደራላዊ ስርአት የአማራን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋጋጠ እንዲሆን፣ የአማራ ህዝብ ትክክለኛ ገጽታው እንዲታወቅና የተዛቡ ገጽታዎቹ እንዲስተካከሉ በጽናት ለመታገል ግልፅ አቋም ተይዟል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአገራችን ህዝቦች በአማራ ህዝብ ላይ ሲካሄድ የነበረውን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ተቋቁመው የአብሮነት እሴታቸውን ጠብቀው በመቆየታቸው ልዩ አድናቆት እና ክብር አለን፡፡

በመሆኑም የአማራ ህዝብ ሁለንተናዊና ዘላቂ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን እየጎለበተና እያደገ በሚሄድ ህብረ-ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነትጠንካራ ኢትዮጵያን ስንገነባ መሆኑን ጉባኤያችን አስምሮበታል፡፡ ስለሆነም የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በዚሁ አቅጣጫ እንዲገነባ በአንክሮ የምንሰራ መሆኑንእናረጋግጣለን!!

3. በአገራችን ተግባራዊ እየተደረገ ባለው የፌደራል ስርዓት የአማራ ህዝብ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች አንገብጋቢ አጀንዳዎች መሆናቸውን ጉባዔያችን በጥልቀት ገምግሟል፡፡ ከማንነትና ከወሰን ጥያቄዎች ጋር የተያያዙና ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች መኖራቸውን በዝርዝር ገምግመናል፡፡ የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ ደግሞ የህዝቡን ነጻ ፍላጎት ከግምት ውስጥ ያላስገባ፤ ህገ-መንግስታዊ ባልሆነና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አግባብ እንዲሁም ልዩነትን የሚያጎላ አከላለል ትኩረት ስለተሰጠው ነው፡፡

በመሆኑም ድርጅታችን አዴፓ ከወሰን አከላልና ከማንነት ጋር የተያያዙ የህዝብ ጥያቄዎች ታሪካዊ ዳራውን ጠብቆ በህዝቡ ነፃ ፍላጎትና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በዘላቂነት ሊያጠናክር በሚችል ሁኔታ በህዝቡ ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ እንዲፈታ የሚጠበቅብንን ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ትግል የምናደርግ ሲሆንከክልላችን ጋር ተያያዥ የሆነውን የአገራችን ኢትዮጵያንና የሱዳንን ድንበር በተመለከተ ሲነሱ የቆዩትን ጥያቄዎች በዝርዝር በመገምገም ቀደም ሲል የነበረውን ግልጽና ህጋዊ ባልሆነ መልኩ የተወሰኑ አካላት ያደረጉት ግንኙነትና ስምምነት ችግር ያለው መሆኑን ስለተገነዘብን በቀጣይነት የፌደራል መንግስታችን መርህ የተከተለና የአገራችን ጥቅም ሊያስከብር በሚችል መልኩ እንዲሁም ከጎረቤታችን ሱዳን ጋር መልካም ጉርብትናችንን አጠናክሮ ሊያስቀጥል በሚችል ሁኔታና ህዝቡን ማዕከል አድርጎ እንዲፈታ እንሰራለን!!

4. ድርጅታችን አዴፓ በጉባዔያችን ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የክልላችን ተወላጆች አያያዝና መብት አጠባበቅ ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚጠይቅ አጀንዳ አድርጎ ገምግሞታል፡፡ የክልላችን ብሄሮችና ብሄረሰቦች አያያዝና ተጠቃሚነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የክልላችን ተወላጆች የፖለቲካ ውክልና፤ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት፤ በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ በነፃነት ተንቀሳቅሰው የመስራት፤ ሃብት የማፍራት፤ ያለመፈናቀል ህገ-መንግስታዊ መብታቸው በተደጋጋሚ ጥሰት ሲፈፀምበት ቆይቷል፡፡ አሁንም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችሞትና መፈናቀል አልቆመም፡፡

በመሆኑም አገራዊ ህገ-መንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን ለዜጎች በየትኛውም አካባቢ ዋስትና የሚሰጥ እንዲሆን ሁለንተናዊ ትግል የሚደረግ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከአጎራባች ህዝቦችና ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እና ወንድማማችነት እንዲጎለብት የምንሰራ ሲሆን የየክልሉ መሪ ፓርቲዎችና መንግስታትየዜጎችን መብት እንዲያስከብሩ፤ የፌደራል መንግስትም የማሻሻያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ድርጅታችን አዴፓ ከእህትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ያላሳለሰ ትግል የሚያደርግ መሆኑን እናረጋግጣለን!!

5. በጉባዔያችን ከልማትና መልካም አስተዳደር ስራችን አንፃር በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማዕቀፍ የዕቅድ አፈፃፀማችን ምን እንደሚመስል በዝርዝር ገምግመናል፡፡በሂደቱም ውጤት የተመዘገበባቸው ተግባራት የመኖራቸውን ያክል አሁንም ትርጉም ባለው መልኩ ድህነትን የመቅረፍ ስራችን፤ የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ፤ ከማህበራዊ ልማት አንፃር የትምህርትና ጤና ተደራሽነትና ጥራት ጉዳይ እና ልዩ ትኩረት የሚጠይቁናበተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃቸውና በተነፃፃሪ የከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙአካባቢዎች የልዩ ዕገዛ ማዕቀፍ ጉዳይ በጥልቀት ውይይት የተደረገበት ሲሆን የዕቅድ አፈፃፀሙም ሰፊ ክፍተት ያለበት መሆኑን ለይተናል፡፡

በመሆኑም የክልላችን አጠቃላይ የልማት ስራዎችን አጠናክረን በማስቀጠል፤ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባር ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ ከትምህርት ተደራሽነትና ጥራት አንፃር መሰረታዊ የሚባሉ ውስንነቶችን በልዩ ርብርብ በመሻገርናልዩ እገዛና ድጋፍ የሚፈልጉ ድርቅ በተደጋጋሚ የሚያጠቃቸውና በተነፃፃሪ የከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ችግሮችን በማቃለል በክልላችን ድህነትን ለማስወገድ የጀመርነውን ትግል አጠናክረን በማስቀጠል የክልሉን ህዝብ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋትና በቁርጠኝነት እንሰራለን!!

6. ድርጅታችን አዴፓ ዋስትና ላለው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የዴሞክራሲ ተቋማት መጠናከር ተኪ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በጥልቀት ገምግሟል፡፡ በግምገማው እንደታየውም የህዝብ ምክር ቤቶች፤ ብዙሃን ማህበራት፤ ሚዲያና የተፎካካሪ ፖለቲካ ሃይሎች በሚፈለገው ልክ የተጠናከሩ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ዋስትና ያለው ዴሞክራሲን ለማረጋገጥ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ጉዳይ ልዩ ርብርብ የሚጠይቅ አጀንዳ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ ስራ ለመስራትና የዜጎችና የቡድን መብቶች ሚዛናቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ እንታገላለን!!

7. ድርጅታችን አዴፓ በዚህ ታሪካዊ ጉባዔ ከድርጅት ግንባታ ጋር የተያያዙና መድረኩን የሚመጥኑ ትላልቅ የለውጥ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ የድርጅቱን መተዳደሪያ ደንብ በማሻሻል ንቅናቄውን ወደ ፓርቲ በማሳደግ የድርጅታችንን ስያሜ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በሚል በመሰየምና ድርጅታዊ ዓርማና ሌሎች የህገ-ደንብ ማሻሻያዎችን አካሂዷል፡፡ በትምህርትና በክብር የተለያዩ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አሰናብቷል፡፡ በተያያዘም አዳዲስ ወጣቶች፤ ሴቶችና ሙህራን አመራሮችን በስፋት ያካተተና መተካካት በተረጋገጠበት ሁኔታ የድርጅት አመራሮችን ሰይሟል፡፡

የድርጅቱን መሰረት የሚያሰፉና የአባላትና አመራሩን ስምሪትና ግንባታ የሚመጥኑ አሰራሮችን ስለሚዘረጉበት ሁኔታ ዝርዝር አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን በማጠናከር አባላት መብታቸውና ነፃነታቸው ተረጋግጦ የሚታገሉበት ድርጅት እንዲሆን የሚያስችሉ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ተላልፈዋል፡፡ በመሆኑም ድርጅታችን አዴፓ የአማራ ህዝብ ሁነኛ ወኪል ሆኖ ህዝቡ የጣለበትን ዕምነት የሚፈፅምና የለውጥ ፓርቲ ሆኖ የክልሉን ህዝብ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን፤ ከዚህም ባሻገር ድርጅታችን አዴፓ ከክልሉም አልፎ በአገራዊ ግንባታ ተልዕኮም የበኩሉን ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኑን እናረጋግጣለን!!

በአጠቃላይ ድርጅታችን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በዚህ ታሪካዊ የለውጥ ሂደት በጉባዔው የወሰናቸውን ውሳኔዎች በብቃት በመፈፀም የአማራን ህዝብ የለውጥ ፍላጎት በብቃት መርቶ ለጠንካራ ህብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ አዴፓ ይህን ወሳኝ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ የምልአተ ህዝቡና የመላ አባላት ርብርብ እንደሚጠይቅ ጉባኤያችን አጽንኦት የሰጠው በመሆኑ እኛ የ12ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የሚከተለውን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የድርጅታችን አባላት፡-

ድርጅታችሁ አዴፓያለፉትን ድክመቶች በማረምና ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በጉባኤው የተጀመረው የጥልቅ ተሃድሶና ክልላዊና አገራዊ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን አስተላልፏል፡፡

ከዚህም አኳያ የለውጡን አቅጣጫና ፋይዳ በአግባቡ ተገንዝባችሁ ለተግባራዊነት የግንባር ቀደም ሚናችሁን በብቃት እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ መላው የአማራ ህዝብ፡- መሪ ድርጅታችሁ አዴፓ በ12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው ካለፉት ስኬቶቹና ድክመቶቹ ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ ወቅቱ የሚጠይቀውን የአመራር ቁመና ለመላበስ የሚያስችሉ ታሪካዊ ውሳኔዎች በማስተላለፍ ብቃት ያለው አመራር ለመስጠት መዘጋጀቱን ሲያበስራችሁ በትላቅ አክብሮትናት የሃላፊነት ስሜት ነው፡፡ ይህ ቁመናችን የክልሉን ህዝብና ከክልሉ ውጪ ብሎም በዓለም አገራት የምትገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ይበልጥ የሚያታግል እንደሚሆን ፅኑ እምነት አለን፡፡ ስለሆነም የድርጅታችን ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁለንተናዊ ተሳትፎአችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ ወጣቶችና ለሴቶች፡-

ድርጅታችን አዴፓ ወጣቶችና ሴቶች ለልማት፣ ለዴሞክራሲና ለሰላም ትግላችን ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ያምናል፡፡ ድርጅታችን አዴፓ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ ፖለቲካ ፓርቲነቱ የሚረጋገጠው በወጣቶችና ሴቶች ብቃት ያለው ተሳትፎ መሆኑንም እንገነዘባለን፡፡ በዚህ ረገድ ባለፉት ግዜያት ተሳትፏችሁንና ተጠቃሚነታችሁን በማረጋገጥ የነበረን እንቅስቃሴ የሚጠበቀውን ያክል ያልነበረ መሆኑን የተገነዘብን ሲሆን በተለይ የስራ አጥነትን ችግር ከማቃለል አኳያ የነበረ አፈጻጸም ደካማ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳትም ጉባኤያችን የወጣቶችና ሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበት የወሰነ በመሆኑ አሁን የተጀመረው ክልላዊና አገራዊ ለውጥ ሳይደናቀፍ የህግ የበላይነት በሚረጋገጥበት አግባብ በብስለትና በማስተዋል ግንባር ቀደም ሚናችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ ምሁራን፡-ምሁራን ለልማትና ዴሞክራሲ አጀንዳዎቻችን የሚጥቅሙ ሃሳቦችን በማፍለቅ ፖለቲካችን ከሃሳብ ድርቀት የሚታደጉ ወሳኝ አቅሞች ናቸው፡፡ የአማራ ህዝብ ማህፀን በርካታ ምሁራንን ያፈራ እንደመሆኑ መጠን ምሁራን በክልላቸው፤ በአገራቸውና በህዝባቸው ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባችኋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለውጡ ትልቅ ተስፋ በማሳደርናድርጅታችን አዴፓና የክልሉ መንግስት ምሁራንን ለማሳተፍ ባሳየው ዝግጁነት ምሁራን በተለያየ መልኩ ህዝባችንን ለማገልገል ያሳያችሁት ጅምር ተግባር የሚያበረታታ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ተሳትፏችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እያቀረብን ምሁራን ፓርቲያችንን በአባልነት በመቀላቀል ፖሊቲካዊ አስተዋፅኦችሁን ጭምር እንድታሳድጉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የመንግስት ሰራተኞች፡- የመንግስት ሰራተኛው የልማት ዋና ፈፃሚያችንና ከህዝቡ ጋር የሚያገናኘን ድልድያችንም ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ባደረግናቸው ትግሎችና አሁን በምንገኝበት የለውጥ መድረክ የህዝባችን ጠያቂነት በከፍተኛ ሁኔታ ከማደጉም በላይ በርካታ ያልመለስናቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በመኖራቸው የመንግስት ሰራተኞች በቅንነት፤ በታማኝነትና በውጤታማነትህዝባችንን በማገልገልና እርካታን በማሳደግ ለውጡን አጠናክረን ለማስቀጠል በምናደርገው ትግል የማይተካ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ሃይሎች፡-

የፈለገውን ያህል በመካከላችን የሚኖሩ የፖለቲካና አስተሳሰቦችና አቋሞች ቢኖሩም መነሻችንና ግባችን የጋራ የሆነውን ክልላችንና አገራችን ጥቅም ከማረጋገጥ ከማሰብ ውጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሁን እንጅ ባለፈው በነበረው ጉዟችን በመካከላችን በጥርጣሬና በጥላትነት የመተያየት አባዜ ተጠናውቶን በመቆየቱ በመድበለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ አሉታዊ ተጽዕኖ ስናሳርፍ ቆይተናል፡፡ በዚህ የለውጥና አንድነትን አጥብቆ በሚሻው መድረክ የፖለቲካ ሃይሎች አንድነት እንጅ የተበታተነና ከመተጋገዝ የወጣ አካሄድ ህዝባችን ይበልጥ የሚጎዳው መሆኑን ጭምር ተገንዝበናል፡፡

በመሆኑም ጉበኤያችን ይህ ሁኔታ ሁላችንም እንደጎዳን በመገንዘብ የተጀመረው ለውጥ ለሁላችንም ጠቃሚ በመሆኑ ሰላማዊና የሃሳብ ትግልን መሰረት በማድረግ በትብብር ለመስራት የተዘጋጀን በመሆኑ በጋራ ለውጡን ዳር ለማድረስና ለውጡ እንዳይቀለበስ በጋራ እንድንስራ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ እህትና አጋር ድርጅቶች፡- የምንገኝበት የለውጥ መድረክ ለልማትና ዴሞክራሲ አጀንዳዎቻችን መሳካት ይበልጥ ምቹ መሆኑን ተገንዝበን ለውጡን አጠናክረን ለማስቀጠል በጉባዔያችን ውሳኔ አሳልፈናል፡፡ በመሆኑም፤ጉባዔያችን ስንጀምር ያሳያችሁትን ፍላጎትና ተስፋ በሚያጠናክር ሁኔታ ድርጅታችን አዴፓ የለውጥ ሃይል ሆኖ ጠንክሮ የወጣ በመሆኑ ለውሳኔያችን ተፈፃሚነት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የትግል አጋርነታችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

የተከበራችሁ የፀጥታ አካላት፡-የፀጥታ አካላት በዚህ በምንገኝበት የለውጥ መድረክ ሰላምና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የከፈላችሁት መስዋዕትነት ክብርና ምስጋና የሚገባው ታላቅ ተግባር ነው፡፡ አሁንም ለውጡን አጠናክረን ለማስቀጠል በምናደርገው ትግል ሰላምንና የህግ የበላይነትን ማስከበር የማይታለፍ ተልዕኮ በመሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ሙያዊ ኃላፊነታችሁን በከፍተኛ ህዝባዊ ስሜትና አደራ እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

የለውጡ ቀጣይነት፤ ለአማራ ህዝቦች ተጠቃሚነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት!

የዐማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)

መስከረም 2011 ዓ.ም

ባህር ዳር፤

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.