Wednesday, April 8, 2020
Home > ዜና > ከ82 በላይ ከቢኒሻንጉል የተፈናቀሉ ዜጎች ሂዎት አደጋ ላይ ነው::

ከ82 በላይ ከቢኒሻንጉል የተፈናቀሉ ዜጎች ሂዎት አደጋ ላይ ነው::

‹‹ከተፈናቃዮች ብዛት አንፃር የድጋፉ ቀጣይነት ያሳስበናል፤ መንግስት ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ሊያፈላልግ ይገባል፡፡ ›› በነቀምቴ የድጋፍ አስተባባሪዎች

ባሕር ዳር፡መስከረም 26/2011 ዓ.ም(አብመድ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች ዘጠኝ የመጠለያ ጣቢያዎች ተዘጋጅተው በዚሁ ከተማ ብቻ ከ82 ሺህ በላይ ዜጎች በጊዜያዊነት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

ለተፈናቃዮቹም የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎችና የከተማዋ ቄሮዎች ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው፡፡ ካለፈው ቅዳሜ መስከረም 19 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በከተማዋ የደረሱት ተፈናቃዮቹ በአካባቢው ህዝብ፣ በወጣቶቹ፣ በከተማ አስተዳደሩ እና በዞኑ አስተዳደር ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ለማየት ችለናል፡፡ ትናንት ጠዋት ተንቀሳቅሰን በጎበኘናቸው ሁለት የመጠለያ ጣቢያዎችም ያረጋገጥነውም ይህንኑ የህዝብ ድጋፍ ነው፡፡

በከተማ ውስጥ ከሚገኙት ዘጠኝ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የነቀምቴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ አንዱ ነው፡፡ በኮሌጁ ውስጥ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ቁጥሩ ከፍና ዝቅ ይበል እንጅ ከ1 ሺህ 200 በላይ ተፈናቃዮች አሉ ያሉን የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ አስተባባሪ አቶ ሚዴቅሳ ገመቹ ናቸው፡፡ ለተፈናቃዮች የወተት፣ የምግብ፣ የአልባሳት እና ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ እና ወልቂጤ ሪፈራል ሆስፒታል ጋር በመተባበር የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጣቸው ነግረውናል፡፡

በነቀምቴ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያ ደግሞ 924 ተፈናቃዮች ይገኛሉ ያሉን የመጠለያ ጣቢያው የሎጀስቲክ ዋና ክፍል ኃላፊ አቶ ተካልኝ ፏ ናቸው፡፡ እንዳቶ ተካልኝ ገለፃና እኛም ተንቀሳቅሰን ለማየት እንደሞከርነው የተሻለ የድጋፍ አገልግሎት እየተደረገላቸው ነው፡፡ ለተፈናቃዮቹ የምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት እና የ24 ስዓት የህክምና አገልግሎት ይደረግላቸዋል፡፡

ለነብሰ ጡሮች እና ከስድስት ወር በታች ያሉ ህፃናትን ለያዙ ተፈናቃዮች ለብቻቸው መጠለያ እንደተዘጋጀላቸው ለማወቅ ችለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወጣት ሴቶች እና ወንዶች ለየብቻቸው የተዘጋጀ ማደሪያ ክፍል ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገዋል ይላሉ አቶ ተካልኝ፡፡

ዛሬ ተንቀሳቅሰን ባየናቸው ሁለቱም ጣቢያዎች እስካሁን የውሃ፣ የመጠለያና የአልባሳት ችግር እንዳላጋጠማቸው አስተባባሪዎቹ ነግረውናል፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ጣቢያዎች ላይ ስጋት አለን ይላሉ፤ እንደስካሁኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተፈናቃዮች ቁጥር የሚጨምር ከሆነ ይህ የህዝብ ደጋፍ እስከመቸ ቀጣይ ይሆናል ይላሉ፡፡ አስተባባሪዎቹ እንደሚሉትም መንግስት ለተፈናቃዮቹ በአፋጣኝ ጊዜያዊ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ በዘላቂነት ግን ዜጎች በፈለጉት አካባቢ በመንቀሳቀስ ሃብትና ንብረት አፍርተው የመኖር ህገ መንግስታዊ መብቶቻቸውን ሊያስከብር ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ጌዳ አያ እና ሊሙ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስተባባሪዎቹ ነግረውናል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው (ከነቀምቴ)

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.