Wednesday, April 8, 2020
Home > ዜና > ኩሪፍቱ ሪዞርት የውኃ መዝናኛ ማዕከል በቅርቡ ለአገልግሎት እንደሚያበቃ አስታወቀ!

ኩሪፍቱ ሪዞርት የውኃ መዝናኛ ማዕከል በቅርቡ ለአገልግሎት እንደሚያበቃ አስታወቀ!

ሪፖርተር- ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ከ15 ዓመታት በፊት በቢሾፍቱ ሐይቅ ዳርቻ የመጀመርያውን ግንባታ በማካሄድ ሥራ ሲጀምር፣ 18 ለቱሪስት ተስማሚ የሆኑና  በአገነባብ ሥልታቸው ለየት ተደርገው የታነጹ ቪላዎች፣ የተንጣለለ  ሬስቶራንትና ባር በማካተት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ዓይነ ግቡ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታቸው አገር በቀል የግንባታ ግብዓቶችን በመጠቀም የታነጹ ከ150 በላይ መኝታ ክፍሎችን በማካተት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ሥራ ሲጀምር ያስተዋወቀው የግንባታ ሥልት አሁንም ድረስ እንደመለያው የሚጠቀምበት ብቻም ሳይሆን፣ ሌሎችም ይኼንኑ በመከተል ተመሳሳይ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል የቻሉበት አጋጣሚ ይታያል፡፡

የቱሪስቶችን ትኩረት ሊስብ የሚችል ገጽታ ይዞ በመቅረብ የአገሪቱን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ጭምር ታስቦ በኩሪፍቱ ሪዞርት የተጀመረው የተደራጀ የሪዞርት አገልግሎት፣ በቢሾፍቱ ሐይቆች ዳርቻ ግንባታዎቹን እንዲስፋፋ ምክንያት ሆነውታል፡፡

ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ለቢሾፍቱ ከተማም ሆነ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ መልካም ገጽታን እንደሚፈጥር የታመነበት ፕሮጀክት በ74 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነባሩ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ ከሚገኝበት አጠገብ እየገነባ ይገኛል፡፡ ‹‹ዋተር ፓርክ›› የሚል መጠሪያ ያለውና ዘመናዊ የውኃ መዝናኛዎችና የኢትዮጵያን ባህላዊ መገልገያዎች ለመሸጥ የሚያስችሉ መደብሮችን ያካተተው የማስፋፊያ ግንባታ፣ ከ100 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተደረገበት እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡  ግንባታውን ሊጠናቀቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ላለፉት ሦስት ዓመታት በግንባታ ላይ የቆየ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ አካል ከሆኑት ውስጥ ገሚሶቹ ሥራ መጀመራቸውም ታውቋል፡፡ የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ መሥራች አቶ ታዲዮስ ጌታቸው እንደገለጹት፣ የዚህ ፓርክ ዓላማ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበርና የጉዞ ፓኬጅ በማዘጋጀት ኢትዮጵያን የምሥራቅ አፍሪካ የቤተሰብ ቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የታሰበበት ነው፡፡

የመዝናኛ ማዕከሉ ለዚህ በሚመጥን ይዘት እንደተገነባ የገለጹት አቶ ታዲዮስ፣ ከመላው ዓለም በሚመጡ ቱሪስቶች የሚፈልጉትን አገልግሎት በአንድ ቦታ አካቶ የሚያቀርብ ማዕከል ዕውን ሊደረግ መቃረቡን አውስተዋል፡፡ ኩሪፍቱ በሚታወቅበት ባህላዊ ዲዛይን መሠረት የተነቡ 205 ቱሪስቶች ሊገበያዩባቸው የሚችሉ ባህላዊ መደብሮች በፕሮጀክቱ ተካተዋል፡፡ ባህላዊ አልባሳትና ሌሎች ምርቶች የሚሸጡባቸው መደብሮች ውጫዊ ዲዛይን በተለመደው ባህላዊ ቁሳቁሶች የተሰደሩ ናቸው፡፡ የመዝናኛ ፓርኩ በአንድ ሰዓት ውስጥ ብቻ ከ1,950 በላይ ቱሪስቶችን ማስተናገድ እንደሚችል ሲገለጽ፣ አራት  ሬስቶራንቶችንም ያካትታል ተብሏል፡፡ የፓርኩ መለያ የሚሆነው ባህላዊ የምግብ አዳራሽም በተለየ ዲዛይን እየተገነባ ይገኛል፡፡

ይህ የውኃ መዝናኛ ማዕከል የኢትዮጵያን ባህል አካቶ ወደ አገልግሎት ሲገባ በአገሪቱ ለመጀመርያ ጊዜ የሚተዋወቅ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ መዝናኛ መንደሩ የተለያዩ የውኃ ላይ መዝናኛዎች በማካተት ለሕፃናትና ለአዋቂዎች የሚስማሙ መዝናኛ በተለያዩ ንድፎች የተዘጋጁ መዝናኛና መጫወቻዎችም አሉት፡፡

እንደ አቶ ታዲዮስ ገለጻ፣ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመርያው የሆነው የመዝናኛ ማዕከሉ፣ አዳዲስ ሐሳቦችን በማካተት የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች በሚያንፀባርቅ መልኩ ከሚገነቡት 205 መደብሮች ውስጥ 95ቱ ለአገልግሎት እንዲበቁ መደረጋቸው ታውቋል፡፡ መደብሮቹ እያንዳንዳቸው ባህላዊ አልባሳትን ጨምሮ የኢትዮጵያውያን የባህል ቁሳቁሶች ለአገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች ያቀርባሉ ብለዋል፡፡ በአገሪቱ የሚገኙ ታዋቂ ዲዛይነሮችንም ያገናኛሉ ተብሏል፡፡ በመደብሮቹ በኩል ምርቶቻቸውን በጋራና በተናጠል በማቅረብ እየሸጡ የሚገኙ ዲዛይነሮች፣ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ጭምር እየተሳፉ የሚገኙ ናቸው፡፡ ዲዛይነሮቹ በፋብሪካና በዕደ ጥበብ ታግዘው እንደሚያመርቱ ተብራርቷል፡፡ ምርቶቹ በማን እንደተሠሩና የት እንደተመረቱ የሚገልጽ መለያ ተደርጎባቸው ለግብይት እየቀረቡ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለአብነትም እግር ጥሎት ወደ መዝናኛው ጎራ ያለ ጎብኚ፣ ከሚመለከታቸው መካከል የባህላዊ ስጋጃ መሸጫ መደብር ማየቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መደብር ውስጥ እያንዳንዱ ስጋጃ በማን እንደተሠራና መቼ እንደተሠራ መግለጫ ያለው ሲሆን፣ ስጋጃውን የሠራው ባለሙያ የሕይወት ታሪክም ከስጋጃው ጋር ተያይዞ የሚሸጥበት ነው፡፡ ሌላኛው መደብር ውስጥ መዓዛማ ዘይቶች ይሸጣሉ፡፡ በዚህ መደብር እንደ እንዶድ ያሉ ባለመዓዛ ዘይቶች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ የከበሩ ማዕድናትን ቀርፆ ጌጣጌጦችን በማበጀት ለሽያጭ የሚቀርብበት መደብርም የመዝኛኛው መገለጫ ነው፡፡ ይህ መደብር ጌጣጌጦችን ቆርጦና አስተክሎ ለመሥራት የሚያስችል ማሽን አለው፡፡ እንደ ኦፓል ያሉ ማዕድናት በጥሬው ከመሸጥ ይልቅ ስሜትን ገላጭና የጥበብ ትሩፋቶች ታክለውበት ለገዥም ለጎብኚም የሚቀርቡበት ነው፡፡

የልጆች የትምህርት ቤት ቦርሳዎች በባህላዊ የአመራረት ሥልት ሊቀርቡ የሚችሉበትን ጥበብ የሚያሳይ መደብርም በማዕከሉ ተከፍቷል፡፡ የኢትዮጵያውያን ዕደ ጥበብ የሚንፀባረቅበት የሸክላ ምርት መሸመት ያማረውም ጎራ ካለ በውኃ መዝናኛ ፓርኩ የልቡን እንደሚያደርስ ይታመናል፡፡

እነዚህ መደብሮች ለየት ባለ መንገድ ሊታዩ የሚችሉበት ሌላው መገለጫቸው ደግሞ፣ እያንዳንዱ ምርት ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ መግለጫ በሁሉም ምርት ላይ በግልጽ መለጠፉ ነው፡፡ ወደ መደብሮች የሚያቀና ገበያተኛ፣ ያለ ውጣ ውረድ ዋጋውን ዓይቶ መግዛት እንዲችል የተደረገ በመሆኑ፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታየውን የዋጋ ድርድር ያስቀራል፡፡

የተለያዩ የውኃ ላይ መዝናኛዎችን የሚያካትተው የፕሮጀክቱ ክፍል በአሁኑ ወቅት ከመሬት በታች የሚገኙ የውኃ ማስተላለፊያ ትቦዎች ተዘርግተው የተጠናቀቁ ሲሆን፣ በሦስት ወራት ውስጥ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ይጠበቃል ተብሏል፡፡ መጫወቻ ክፍሎቹ ለፓርኩ የተለየ ገጽታ በሚያላብሱና ለውኃ መዝናኛ ሥፍራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተሟልተው በመቅረባቸውና ሌሎቹም የማጠናቀቂያ ሥራዎች ተከናውነው ይህ የፕሮጀክቱ ክፍል በጥቂት ወራት ውስጥ  ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡

ወደ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ወደ ዋተር ፓርኩ የሚመጣ ጎብኚ፣ ጠይቆ የሚያጣው ነገር ምንም እንዳይኖር ታስቦ የተቀረፀው ይህ ፕሮጀክት፣ የባንክ አገልግሎት እንዲሰጡም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና እናት ባንክ ከወዲሁ አገልግሎታቸውን ማቅረብ እንደጀመሩም ማየት ተችሏል፡፡ የባንኮቹ ውስጣዊ ገጽታ የኩሪፍቱን መገለጫ ባህላዊ ዲዛይንና ጠረጴዛዎችና ተያያዥ መገልገያዎችን የሚያሳዩ መሆናቸውም ቀለሙን አጉልተውታል፡፡

ፕሮጀክቱ በከተማችን የሚታወቁና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ውስጥ የተሠማሩ ኩባንያዎችን የሚያካትት በመሆኑ፣ እየተጠናቀቁ ባሉ መደብሮች ውስጥ ካልዲስ ካፌ፣ ቶሞካ ቡናን ጨምሮ ሌሎችም አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚሳተፉበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዲዛይነሮች ባሻገር ሠዓሊያንም የሥዕል ውጤቶቻውን ለጎብኚዎች በማቅረብና በሚሸጥ የሚሳተፉበት ቦታም ተዘጋጅቷል፡፡ እስካሁንም 20 ሠዓሊያን ሥዕሎቻቸውን የመሸጥ ዕድል እንዳጋጠማቸው ተነግሯል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስን የመሰሉ የቢራ ፋብሪካዎችም ቢራ የሚሸጡበት መናፈሻ ይኖራቸዋል፡፡ እንደውም በ54 የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚመረቱ የቢራ ዓይነቶችን በመዝናኛ ማዕከሉ ውስጥ ለማቅረብ የሚችሉበት የንግድ ዘርፍ እየተመቻቸ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዲያጆና ኮካ ኮላን ጨምሮ ሌሎች የመጠጥ ፋብሪካዎችም በማዕከሉ የራሳቸውን ቦታ ይዘው የሚሠሩበት ስምምነት ተፈጥሯል፡፡

ፕሮጀክቱ መሠረታዊ ዓላማ አገር ማስተዋወቅ በመሆኑ፣ የውኃ መዝናኛ ፓርኩ ኢትዮጵያን በአንድ ባህላዊ መንደር ውስጥ በሚያሳይ አንድ ሥፍራ ላይ በመደዳ  የአገሪቱን ባህላዊ መጠጦች ለማስተዋወቅ ይረዳ ዘንድ ጠላ ሲጠመቅ፣ አረቄ ሲወጣ፣ ጠጅ ሲጣል የሚታይበት ቦታ ያለው ሲሆን፣ ጎብኚዎች ወደዚህ ሥፍራ በመሄድ የመጠጥ አዘገጃጀቱን እየተመለከቱ ባህላዊ መጠጦችን ‹‹ለጤናችን›› የሚባባሉበት ሥፍራም መዘጋጀቱን የኩባንያው ኃላፊ ገልጸዋል፡፡ ለባህላዊ መጠጦች የማዘጋጃ ሥፍራው ግንባታም በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ ፓርክ የሚጠበቀው ሌላው የመዝናኛ ሥፍራ፣ በጎጆ ቅርፅ እየተገነባ የሚገኘው ግዙፍ ባህላዊ የምግብ አዳራሽ ነው፡፡ ባህላዊ ምግብ ቤቱ ከኢትዮጵያ ምግቦች አንድም ሳያስቀር አዘጋጅቶ የሚቀያቀርብ እንደሚሆንም ተጠቅሷል፡፡

ኩሪፍቱ በባለቤትነት ከሚያስተዳድራቸው ሪዞርቶች ባሻገር በሽርክና የሆቴል  አስተዳደር ስምምነት አማካይነት የሚያስተዳድራቸው ሆቴሎችና ሪዞርቶች በሥሩ እያስተዳደረ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.