Wednesday, April 1, 2020
Home > ዜና > የላሊበላ ውቅር አብያተክርስትያን አደጋ ላይ ነው!

የላሊበላ ውቅር አብያተክርስትያን አደጋ ላይ ነው!

የላሊበላ ነዋሪዎች በውቅር አቢያተ ክርሰቲያናቱ ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳት ትኩረት ባለመሰጠቱ ሰላማዊ ሰልፍ ሊውጡ ነው፡፡

(አብመድ) – የአቢያተ ክርሰቲያናቱ ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ጊዚያዊ መጠለያዎቹም ተጨማሪ ስጋት መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህ እየታወቀ ግን ትኩረት በማጣቱ የአካባቢው ህብረተሰብ የላሊበላን ቅርሶች እንታደግ በሚል መሪ ሃሳብ መስከረም 27 ትዕይንተ ህዝብ ያካሂዳሉ፡፡

የሀገራችን የቀደምት የጥበብ ባለቤትና የከፍታዋ ዘመን መለኪያ እና ማሳያ ናቸው፣

ከእጅ ወደ አፍ ለሚያመርተው ለአርሶ አደሩ፤ ምንም ፋብሪካ ለሌለው ለከተማው ነዋሪ ብቸኛ የአይን ማረፊያ፤ የመንፈስ ማደሻ ዋ ብሎ መጉረሻ እና ህይዎት ናቸው፡፡ የላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች ከ80 በመቶ በላይ የላሊበላ ውቅር አቢያተክርስቲያናትን ታሳቢ አድርገው እንደሚገቡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

እነዚህ ላለፉት 800 ዓመታት መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አቢያተክርስቲያናት ዛሬ ላይ በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ጉዳት ደርሶባቸዋል እየደረሰባቸውም ይገኛል፡፡

አቢያተክርሰቲያናቱ ከውጭ በተገኘ እርዳታ እስካሁን ሶስት ጊዜ ጥገና ተድርጎላቸዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን ጉዳቱን በዘላቂነት መከላከል አልተቻልም፡፡ በተለይም በቅርቡ የተሰራው መጠለያ የመሰሶዎቹ ክብደት ከፍተኛ መሆን እና ዋሻ ላይ መቆማቸው፤ በአካባቢው ያለው የንፋስ ፍጥናት በመጨመሩ የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎች እና ድምፅ የስጋት ምንጮች ሆነዋል፡፡

ከ5-7 ዓመት አገልግሎት መስጠት የነበረበት መጠለያ ከ10 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ ይህም አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል የቅርስ ባለሙያዎቹ ጥናት አመልክቷል፡፡

በነዚህ ችግሮች ላይ ከሚመለከታቸው አካል ጋር መግባባት ቢደረስም ውሳኔ ባለመገኘቱ የአካባቢው ህብረተሰብ “የቅዱስ ላሊበላ ቅርሶችን እንታደግ” በሚል መሪ ሃሳብ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያካሂድ መሆኑን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝም ወጣት ስፖርት ፅ/ቤት ኃላፊና ም/ከንቲባ አቶ ሀይሌ ንጋቴ ተናግረዋል፡፡

እስከ ፌዴራል ባለው የመንግስት መዋቅር ብሎም እስከ የተባበሩት መንግስታት የሳይንስ፣ የትምህርትና ባህል ማዕከል (ዩኒስኮ) ለዓመታት ውይይት ተደርጎ ለጥገናውና አሁን ላለው መጠለያ ማስነሻ ከ300 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ መሆኑን በባህልና ቱሪዚም በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ተገልጧል፡፡ በዚህ ዓመትም ስራ ይጀምራል የሚል ተስፋ የተሰጠ መሆኑን የተናገሩት በኢ/ኦ/ተ/ቤ የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ አባ ፅጌ ስላሴ መዝገቡ ባለፉት ዓመታትም ቃል ተገብቶ ባለመተግበሩ ጩኽታችን እያሰማን ነው ብለዋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፉ ለየት ባለ መንገድ እንዲካሄድ ቤተክርስቲያኗ እየሰራች መሆኗን አባ ፅጌ ሥላሴ ተናግረዋል፡፡

ም/ከንቲባው አቶ ሃይሌም ትልቁ ሃብታችን እና ፋብሪካችን ቅርሳችን ነው ሁላችንም ድምፃችን ማሰማት አለብን ብለዋል፡፡

ሰልፉ ሰላማዊ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ የገለፁት የላሊበላ ከ/አስ የመንገድ ትራፊክ ዋና የስራ ሂደት ኢንስፔክተር ታደሰ አማሪው በተለይ ወጣቶች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

የፊታችን እሁድ መስከረም 27 በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ፤ ታሪክ መስራት ባንችል ታሪክ እንጠብቅ፤ መንግስት የማያውቃት ግን ዓለም የሚያውቃት ከተማ ላሊበላ፤ ዝምታ ይሰበር ፣ ተስፋ ያብቃ ስራ በተግባር ይደገፍ የሚሉና ሌሎች መፎክሮች እንደተዘጋጁ ከዝግጅት ኮሚቴው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዘጋቢ፡-መኮንን ዘገየ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.