Monday, March 30, 2020
Home > ዜና > በየአካባቢው የታጠቁ ኃይሎች እየተፈጠሩ ነው!

በየአካባቢው የታጠቁ ኃይሎች እየተፈጠሩ ነው!

ኮንጎ፣ ማዕካላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ የመን ወዘተ መንግሥት አልባ የሆኑት ከመንግሥት ውጭ የሆኑ ሕዝብን የሚያሸብሩ ከማዕከላዊው መንግሥት ያፈነገጡ የታጠቁ ኃይሎች [warlords] በመፈጠራቸው ነው። ከማዕከላዊው መንግሥት የሚያፈነግጡ የታጠቁ ኃይሎች [warlords] የሚፈጠሩት በአንድ ጊዜ አይደለም። በአንድ ቦታ አንድ ሕዝብን የሚያሸብር የታጠቀ ኃይል [warlor] በተፈጠረ ቁጥር የዚህን የታጠቀ ኃይል ጥቃት ወይንም በሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን ሽብር ለመመከትና አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ሲል ሌላ የታጠቀ ኃይል [warlord] ይፈጠራል። ይህ ትርምስ በራሱ ኃይል እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ይሄድና አገሪቷ በየአካባቢው በታጠቁ ኃይሎች [warlords] ቁጥጥር ሥር ትወድቃለች።

ኦነግ በእድሜ ዘመኑ ሕጻናትና ሴቶችን፣ አቅመ ደካሞችንና ሰላማዊ ዜጎችን ሲገድል፣ ሲያፍንና ሲዘርፍ እንጂ አንድም ጊዜ ከታጠቀ ኃይል ጋር ገጥሞ ጦርነት ያካሄደበት ወቅት የለም። አገር ለማፍረስ ካልሆነ በስተቀር እድሜ ልኩን ሕጻናትን፣ ሴቶችን፣ አቅመ ደካሞችንና ሽማግሌዎችን ሲገድል፣ ሲያፍንና ሲያፈናውል የኖረው ኦነግ እንደታጠቀ የሚንቀሳቀስበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። ባለፈው ሳምንት መለስ ዜናዊ የፈጠረውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ የጸጥታ ኃላፊዎች የኦነግ ኃይሎ በመግደላቸው የተነሳ ይህንን ጥቃት ለመበቀል ቤንሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ አዲስ የታጠቀ ኃይል [warlor] ተፈጥሮ የበቀል እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው። ይህ ነገ በሌላው አካባቢም ይቀጥላል። ቆራጥ መሪ ተፈጥሮ በየአካባቢው እየተፈጠሩ ያሉ እንደ ኦነግ አይነት እድሜ ዘመናቸውን ሕጻናትና ሴቶችን፣ አዛውንትና አቅመ ደካሞችን ሲገድሉ የኖሩ ሕዝብን የሚያሸብሩ የታጠቁ ኃይሎችን [warlords] ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ በቶሎ ትጥቅ ማስፈታት ካልቻለ ሶማሊያ፣ ሊቢያ፣ ኮንጎ፣ ወዘተ ያጋጠማቸው እድልና መወጣት ወደማንችለው አዘቅት ውስጥ በቅርቡ መግባታችን አይቀሬ ነው።

እስካሁን ድረስ ያየነው መንግሥት የሚባለው አካል ኦነግ የሚባለው የሴቶችና የሕጻናት ጨፍጫፊ ቡድን በማዕከላዊ መንግሥቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጦ «ትጥቄን የሚያስፈታኝ አካል የለም» እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ እንደ ስለት ልጅ አቅፎ ደግፎ እሹሩሩ ሲልና ያለመጠን ሲንከባከብ ነው። ይህ በመንሥትነት የተሰየመው አካል ከመጠን ያለፈው እንክብካቤ የጦርነት ባላባት በመሆን ቆራጭ ፈላጭ ሆኖ እድሜውን መግፋት የሚፈልገውን ዳዎድ ኢብሳን ልቡን አሳብጦት ከማላውቀው ፍቅር የማውቀው ጥላቻ ይሻለኛል ብሎ አሻፈረኝ በማለት በያካባቢው ያሰማራው የኦነግ ሰራዊት በሰላማዊ ሰዎች ላይ እያካሄደው ባለው ሽብርና ጭፍጭፋ ከማዕከላዊ መንግሥት ውጭ የሆኑ የታጠቁ ኃይሎች [warlords] እንደ እንጉዳይ በአንድ ሌሊት በቅለው ማደር ጀምረዋል። ከታች በዜና እወጃው ላይ ሲነሳ የምትሰሙት የታጠቀ ኃይል ኦነግ በሕዝብ ላይ ሲያካሂድ የሰነበተውን ሽብር ለመመከት ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚባለው የመለስ ዜናዊ ክልል ውስጥ የተፈጠረና እስካሁን ድረስ ማንነቱ ያልገለጠ የታጠቀ ኃይል ነው።

የምስራቅ ወለጋው የጸጥታ ኃላፊ ይህ የታጠቀ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ ሲጠይቅ ይሰማል። ኦነግ ትጥቁን እስካልፈታና በሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ሽብር እስካልቆመ ድረስ ሌላው በኦነግ ጥቃት የሚፈጸምበት ትጥቅ እንዲፈታ መጠየቅ ነውረኛነት ነው። ኦነግ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጠረ ያለውን ሽብር ለመመከር በቤብሻንጉል ጉሙዝ ብቻ ሳይሆን በጋምቤላው ለጊዜው ራሱን ይፋ ያላደረገ ታጣቂ ኃይል መፈጠሩ ተሰምቷል።

ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም/ጎንደር/ሱዳን በሚወስደው መንገድ ከአዲስ አበባ 170 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቱሉ ሚልኪ አካባቢ ቅዳሜ እለት ከ10:00 ሰዓት ጀምሮ መንገዱ ከሁለቱ አቅጣጫ ተዘግቶ ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎች ታግተው ሰላማዊ ሕዝብ ሲሸበር አምሽቷል። በመንግሥትነት የተሰየመ አካል የሕዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻለ በዚህ አካባቢ ወዲህና ወዲያ ማዶም ራሱን ከሽብር ለመከላከል የታጠቀ ኃይል መፈጠሩ የማይቀር ነው። በምሥራው በኩል የሚታወቀው ኦብነግም ሰራዊቱን ማሰባሰብ መጀመሩ እየተሰማ ነው። ኦነግ ታጥቆ በየአካባቢው ሰላማዊ ሕዝብን ማሸበሩን እስከቀጠለ ድረስ በሌሎች የአገራችን አካባቢዎችም እንደ ቤንሻንጉሉና ጋምቤላው አይነት አዳዲስ የታጠቁ ኃይሎች[warlors] ሳይውል ሳያድር መፈጠራቸው አይቀሬ ነው።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.