Wednesday, April 8, 2020
Home > ዜና > ከአዲስ አበባ ግብረ ሀይል የተሰጠ መግለጫ!

ከአዲስ አበባ ግብረ ሀይል የተሰጠ መግለጫ!

ከተማችን አዲስ አበባ ለአያሌ ዘመናት የመቻቻል የአብሮ መኖርና የፍቅር ተምሳሌት ብሎም የተለያዩ አለም አቀፍና ሀገራዊ ጉባኤዎችን የምታስተናግድ አህጉራዊት ርእሰ ከተማና የኢትዮጵያን መገለጫዎች ሁሉ ተሸክማ የያዘች ትንሿ ኢትዮጵያ በመሆን ቆይታለች ይህም የሆነው በከተማዋ ተወላጆች(አዲስ አበቤዎች) ሰላም ወዳድነት የሰለጠነ ፖለቲካ ፈላጊነትና መልካም ፈቃድ መሆኑ ይታወቃል

ይሁንና ከዚህ የአዲስ አበቤዎች ሰላም ወዳድነትና የሀሳብ ፖለቲካ ፍላጎት በተፃራሪ የአዲስ አበባን የጋራ ርእሰ ከተማነትና የተወላጆቿን ህጋዊ ባለመብትነት ባላከበረ መልኩ “አዲስ አበባ የኛ ናት” በሚል ምክንያት የአዲስ አበባን ሰላማዊ ነዋሪ ሽብር ውስጥ መክተትና መድረሻ ቢስ አድርጎ መቁጠር ብሎም “በዚህ ከተማ በቁጥር ብዛት የኛ ይበልጣል ስለዚህም የኛ ታሪካዊ ርስት ናት” በማለት ከተማይቱን በሽሚያ የምትወሰድ ባለቤት አልባ ማድረግ የዘመኑ የዘረኞችና ፖለቲከኛ ነን ባዮች ፋሽን ሆኗል

የአዲስ አበባ ህዝብ ያልኖረበትንና ያላደገበትን ጎሰኝነት አልቀበልም በማለቱና ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀኑም በመንግስት በኩል በተጠና መንገድ የአዲስ አበባ ወጣት ስራ አጥ ሱሰኛ ሀገሩን ጥሎ በስደት የሚቅበዘበዝ እንዲሆን ሲሰራ ከመቆየቱም በላይ በሀገሩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንዳይሳተፍ ሲገፋ ቆይቷል ይህ ሁሉ እየተደረገበትም አዲስ አበቤው ዋጋ በሚያስከፍሉ ሀገሩን ጉዳዮች ላይ ጭምር በመሳተፍ ሀገሩን ሲጠብቅ ኖሯል

በቅርቡም “አዲስ አበባ የኛናት” በሚሉ ከአዲስ አበባ ውጪ በመጡ ወጣቶች በተጫረ ፀብ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፀቡን በፍቅር ለማብረድ በመሞከር በወቅቱ ወደ ሀገር ቤት ይገቡ ለነበሩት የኦነግ መሪዎች አቀባበል ለመጡ ዜጎች ምግብና ውሀ በማቅረብ በሰላም እንዲያልፍ አስተዋፅኦ ያደረገ መሆኑ እየታወቀ እንደ ፀብ አጫሪ ተቆጥሮ በተለያዩ አካላት ጥቃት ተሰንዝሮበታል ጥቃቱን አስቁሙልኝ ብሎ አደባባይ በመውጣት መንግስትን ሲማፀንም ከፀጥታ ሀይሎችም ህገወጥ ግድያ የተፈፀመበት ከመሆኑም በላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ የከተማዋ ወጣቶች በጅምላ ታፍሰው የደረሱበት አልታወቀም አሁንም ወጣቶች እየታደኑ ይገኛሉ

የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየተወያዩ ነው ቢባልም የሚወያዩት በእድሜም ሆነ በነዋሪነት የከተማዋ ወጣቶች ካልሆኑ ግለሰቦች ጋር ሲሆን የስብሰባ ጥሪውም የሚከናወነው በምስጢርና በቀበሌ ተሳትፎ መመዘኛነት ብቻ መሆኑም በከተማዋ ላይ አሁንም ግልፅ ያልሆነ ሸፍጥ እየተሰራ መሆኑን ያሳያል በመሆኑም

1.ከአዲስ አበባ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የታፈኑ ወጣቶች በአስቸኳይእንዲፈቱ እንጠይቃለን

2.መንግስት በአዲስ አበባ ጉዳይ ወሳኙና ህጋዊ ባለመብቱ አዲስ አበቤ መሆኑን ተረድቶ በከተማዋ ጉዳይ ከከተማዋ ህዝብ ጋር እንዲመክር እየጠየቅን አዲስ አበባን ከማይወክሉ ግለሰቦች ጋር በመወያየት ከአዲስ አበባ ህዝብ ጋር ተወያይተናል የሚል ሸፍጥ እንዲቆም እንጠይቃለን

3.በቅርቡ በተከሰተው ግጭት በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ጉዳት ያደረሱ ግለሰቦችና የፀጥታ ሀይሎች ጉዳዩ ተጣርቶ ለህግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን

4.የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው በአዲስ አበባ ጉዳይ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን የሚናገሯቸውን የከተማውን ነዋሪ ህጋዊ ባለመብትነትና የነዋሪውን ክብር ያልመጠነ ንግግር በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን

5.መላው የከተማዋ ነዋሪዎችም በተለይም ወጣቶችና ምሁራን የአዲስ አበባን ጥያቄዎች ለመንግስት የሚያቀርብ ኮሚቴ ማዋቀርና ከተማይቱን የሚወክል ተቋም ምስረታ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን

6.በከተማችን ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጫናና ወከባ የማይቆም ከሆነም ይህ እንዲቆም ለመጠየቅ በምናደርገው ህጋዊ ትግል መላው አዲስ አበቤ ከጎናችን እንዲቆም እንጠይቃለን

ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.