Wednesday, April 8, 2020
Home > ጤና > ስለ የደም ማነስ በሽታ ምን ያህል ያውቃሉ?

ስለ የደም ማነስ በሽታ ምን ያህል ያውቃሉ?

የደም ማነስ(Anemia)

የደም ማነስ በደምዎ ውስጥ በቂ የሆነ ጤናማ ቀይ የደም ሴሎች ወይም ሄምግሎቢን ሲያንስ የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ ሄሞግሎቢን ዋናው የደም ሴሎቻችን ክፍል ሲሆን ከኦክስጅን ጋር ይጣመራል በጣም ጥቂት ወይም ጤናማ ያልሆኑ ቀይ የደም ሴሎችን ካሉን ወይም ጤናማ ያልሆነ ጥቂት ሄሞግሎቢን ካለን በሰውነታችን ውስጥ ያሉት ሴሎች በቂ ኦክስጅን አይደርሳቸውም፡፡ የደም ማነስ ምልክቶች ከሆኑት አንዱ የሆነው የድካም ስሜት የሚከሰተው የሰውነት አካሎቻችን በትክክል ለመስራት የሚፈልጉትን ያክል ኦክስጅን ስለማያገኙ ነው፡፡

ሴቶች ህፃናት እና ከባድ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ለደም ማነስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ልናስታውሳቸው የሚገቡ ጠቃሚ ነገሮች እነሆ፦

✔አንዳንድ የደም ማነስ አይነቶች በዘር የሚተላለፉና በወሊድ ጊዜ ህፃናትን የሚያጠቁ ናቸው፡፡

✔ለአቅመ ሂዋን የደረሱ ሴቶች በብረት እጥረት ለሚከሰተው የደም ማነስ በተለየ ሁኔታ የተጋለጡ ናቸው ምክንያቱም በወር አበባ ጊዜ የደም መፍሰስ እና በእርግዝና ወቅት የደም ፍላጎት ስለሚጨምር ነው፡፡

✔በእድሜ የገፉ ሰዎች በደም ማነስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው ምክንያቱም በምግብ እጥረት እና የተለያዩ የህክምና ችግሮች ስለሚኖሩባቸው ነው፡፡

የተለያዩ የደም ማነስ አይነቶች አሉ ሁሉም የተላያዩ መነሻ እና የተለያየ ህክምና አላቸው፡፡ በብረት እጥረት የሚከሰተው የደም ማነስ በጣም የተለመደ በሽታ ነው አመጋገባችንን በመቀየር እና የብረት ንጥረ ነገር በመዉሰድ በቀላሉ መታከም እንችላለን፡፡ አንዳንድ የደም ማነስ አይነቶች ለማሳሌ በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው ጤናማ ነው አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ እድሜ ልክ የሚዘልቁ ናቸው፡፡

የደም ማነስ መነሻ ምክንያቶች

ከ400 የሚበልጡ የደም ማነስ አይነቶች አሉ እነሱም በሶስት መደቦች ይከፈላሉ፦

1. በደም መፈሰስ የሚከሰት

2. ቀይ የደም ሴሎች ምርት መቀነስ ወይም የማምረት ችግር

3. በቀይ የደም ሴሎች ውድመት/ጥፋት የሚከሰት የደም ማነስ አይነቶች ናቸው፡፡

1. በደም መፍሰስ የሚከሰት የደም ማነስ

ደም በሚፈሰን ጊዜ ብዙ ቀይ የደም ሴሎችን እናጣለን ይህም የሚከሰተው በትንሹ ለረጂም ሰዓት ደም ስለሚፈሰን ሲሆን ይህን ነገር ብዙ አናስተዉለውም፡፡ እንደዚህ አይነቱ ከባድ የደም መፍሰስ በሚከተሉት መንገዶች ይከሰታል

✔ ከጨጓራና አንጀት ጋር የተያያዘ በሽታዎች (ክንታሮት፣ቁስለት፣የጨጓራ ህመም እና ካንሰር)

✔ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች(አስፕሪን ወይም አይቡፕሮፊን)

✔ የወር አበባ እና በወሊድ ጊዜ(በተለይ በወር አበባ ጊዜ የደም ፍሰት ከመጠን በላይ ከሆነ እና በተደጋጋሚ እርግዝና ከተከሰተ)

2. ቀይ የደም ሴሎች ምርት መቀነስ ወይም የማምረት ችግር::

በዚህ አይነት የደም ማነስ ጊዜ ሰዉነታችን በጣም ጥቂት የደም ሴሎች ማምረት ወይም የደም ሴሎቻችን በትክክል ተግባራቸውን መወጣት ሲያቅታቸው ሲሆን በሁለቱም አጋጣሚዎች የደም ማነስ ይከሰታል፡፡ ቀይ የደም ሴሎች ችግር ይኖርባቸዋል ወይም በቁጥር ይቀንሳሉ የዚህ ምክንያት ጤናማ ያልሆኑ የደም ሴሎች ሲኖሩ ወይም ተግባራቸውን በብቃት ለመወጣት የሚያገለግሉ ሜኔራሎችና ቫይታሚኖች እጥረት ሲኖር ነው፡፡ ለዚህ አይነቱ የደም ማነስ መነሻ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፦

✔ ሲክል ሴል የደም ማነስ(አኒሚያ)

✔ በብረት እጥረት የሚመጣ የደም ማነስ

✔ በቫይታሚን እጥረት

✔ በመቅኒ እና አባት/መነሻ ሴል ችግር

✔ ሌላ የጤና ችግሮች ናቸው

በሲክል ሴል የሚከሰት የደም ማነስ በዘር የሚተላለፍ ሲሆን ቀይ የደም ሴሎች የጨረቃ ቅርጽ እንዲኖራቸው ያደርጋል ስለዚህ በቂ ኦክስጂን ወደተለያዩ አካሎች ማድረስ ያቅተዋል፡፡ የጨረቃ ቅርጽ ያላቸው የደም ሴሎች በጥቃቅን የደም ቧንቧዎች ውስጥ ይቀረቀራሉ ይህም ህመም ያስከትላል፡፡

በብረት እጥረት ምክንያት የሚከሰተው የደም ማነስ ብረት በተባለው ሚኒራል እጥረት ሲኖር ነው፡፡ በአጥንታችን ውስጥ ያለው መቅኒ ኦክስጂን ወደተለያዩ የሰውነት ክፍል የሚደርደውን ሄሞግሎቢን ለመስራት ብረት ያስፈልገዋል፡፡ በቂ የሆነ የብረት ሜኔራል ከሌለ በቂ የሆነ ሄሞግሎቢን አይመረትም የዚህ ውጤት በብረት እጥረት የሚከሰት የደም ማነስ ነው፡፡ የዚህ አይነቱ የደም ማነስ መነሻ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው::

✔ የብረት እጥረት ያለባቸው ምግቦችን የመመገብ ዘይቤ

✔ እርግዝና እና ማጥባት የእናትን የብረት ክምችት መጠን ይቀንሳል

✔ የወር አበባ

✔ በተደጋጋሚ የደም ልገሳ ማድረግ

✔ ከባድ ስፖርታዊ ልምምዶች

✔ የምግብ መፍጨት ችግሮች

✔ አንዳንድ መድሃኒቶች

በቫይታሚን እጥረት የደም ማነስ የሚከሰተው በቫይታሚን ቢ 12 እና ፎሌት እጥረት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ቫይታሚኖች ቀይ የደም ሴሎችን ለመስራት ያገለግላሉ፡፡ ለዚህ ችግር መነሻ ምክንያቶች

✔ ሜጋሎብላስቲክ አኒሚያ፡ የቫይታሚን ቢ12 እና ፎሌት እጥረት

✔ ፐረንሸስ አኒሚያ፡ የቫይታሚን ቢ12 በጨጓራ የመመጠጥ ችግር ነው

✔ የምግብ እጥረት፡ ትንሽ ስጋ ወይም ሙሉ ለሙሉ ስጋ አለመመገብ

✔ እርግዝና፣ አንዳንድ መድሃኒቶች፣ የአልኮል ሱሶች፣ የአንጀት በሽታዎች

አፕላስቲክ አኒሚያ፡ አባት(መነሻ)ቀይ የደም ሴሎች በቁጥር ሲቀንሱ ነው

✔ ታላሲሚያ የሚከሰተው ቀይ የደም ሴሎች በትክክል መብሰል እና ማደግ ሲያቅታቸው ነው

✔ ሊድ ለተባለው መርዛማ ማዕድን መጋለጥ የአጥንት መቅኒ እንዲጎዳ ያደርገዋል

በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት የደም ማነስ መነሻው ለቀይ የደም ሴሎች ምርት የሚጠቅሙ ሆርሞኖች እጥረት ሲሆን በዚህ አይነት ምክንያት የሚከሰቱት የሚከተሉት ናቸው::

✔ ከባድ የኩላሊት በሽታ

✔ የታይሮይድ እጥረት

✔ የተለያዩ በሽታዎች(ስኳር፣ ካንሰር፣ ሪህ፣ ኢንፌክሽን)

✔ የእድሜ መግፋት

3. በቀይ የደም ሴሎች ውድመት/ጥፋት የሚከሰት ደም ማነስ:-

ቀይ የደም ሴሎች በሚሰባበሩበት ጊዜ እና የደም ዝዉዉር ውጥረት መቋቋም ሲያቅታቸው ያለ እድሜያቸው ይፈነዳሉ ከዚያም ሄሞላይቲክ አኒሚያ ይከሰታል፡፡ ይህ ችግር ስንወለድ ወይም ካደግን በኃላ ሊከሰት ይችላል አንዳንድ ጊዜ መነሻ ምክንያቱ አይታወቅም፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.