Wednesday, April 8, 2020
Home > ዜና > አዲስ አበባዎች አስደናቂ ተግባር ፈፀሙ!

አዲስ አበባዎች አስደናቂ ተግባር ፈፀሙ!

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከቤኒሻንጉል ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የለገሱት የስቸኳይ እርዳታ ለኦሮሚያ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት እና ለብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በዛሬው እለት አስረክበናል።

በባለሙያዎች ከ3.8 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተው አስቸኳይ የምግብ እና የአልባሳት እርዳታ፤ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በመደባቸው ሁለት የማጓጓዣ ከባድ መኪኖች ላይ የተጫኑ ቢሆንም፤ ከአንድ ተጨማሪ መኪና በላይ የሚፈጅ ቁሳቁስ በመቅረቱ በሁለተኛ ዙር ለመውሰድ ተስማምተናል።

በዚህም መሰረት እስከ ፊታችን አርብ ድረስ ተጨማሪ እርዳታ ለመለገስ ተነሳሽነቱ ያላችሁ ወገኖቻችን፣ ሀገር ፍቅር ቴአትር ድረስ በመገኘት ለመርዳት አጋጣሚውን ትጠቀሙ ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።

የአዲስ አበባ ነዋሪ የቅስቀሳ ዘመቻውን ከ90 በመቶ በላይ በማህበራዊ ሚዲያ በመስማት ያሳየው ፈጣን ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን እየገለጽን፤ (ሼር እና ፖስት በማድረግ መረጃውን ያሰራጫችሁ ቅን ኢትዮጵያዊያን ካደረጋችሁት ርብርብ በተጨማሪነትም) በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የቅስቀሳ ዘመቻው አጋር ለሆናችሁ የሚዲያ አባላት በሙሉ በተለይም ለታዲያስ አዲስ የራዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች ያለንን የከበረ ምስጋና ማቅረብ እንወዳለን።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለቤኒሻንጉል ተፈናቃይ ወገኖቻችን ያደረጋችሁት ልብ የሚነካ በጎ ምግባር ለታቀደው አላማ መዋሉን ለመታዘብ ተዋናይ ኑረዲን ነስሮ የተባለ የአስተባባሪ ኮሚቴው አባል በነገው እለት የእርዳታ ምግቦችና ቁሳቁሶችን ከያዙ ተሽከርካሪዎች ጋር ነቀምት ወደሚገኙት መጠለያ ጣቢያዎች ያመራል።

ከአስተባባሪ አባላት በተጨማሪ ጥሪያችንን ሰምታችሁ እስከ ማታ ድረስ የጉልበት ስራ ላይ ተሳትፎ በማድረግ ስትደክሙ ለዋላችሁ የመልካም ልብ ባለቤት ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የከበረ ምስጋናችንን እናቀርባለን።

የሐገር ፍቅር ቴአትር ስራ አስኪያጅ፤ የቴአትር ቤቱ ሰራተኞች እና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ ለነበራችሁ የጎላ ሚና የላቀ ምስጋናችን ይድረሳችሁ።

ጥሪያችንን አክብራችሁ፤ ልብ የሚነካ በጎ ተግባር የፈፀማችሁ፤ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሰጣችሁ፤ እናንተ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች ቡሩካን ሁኑ።

ቸር ወሬ ያሰማን

#ቅድሚያ_ለሰብዓዊነት!!

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.