Wednesday, April 1, 2020
Home > ዜና > በእንቅልፍ ልብ መታፈን (Sleep Apnea) እንዴት ይከሰታል? መፍትሄዎቹ::

በእንቅልፍ ልብ መታፈን (Sleep Apnea) እንዴት ይከሰታል? መፍትሄዎቹ::

በእንቅልፍ ልብ መታፈን ማለት አንድ ሰው በእንቅልፍ ልብ ሆኖ ከአሥር ሰኮንድ እስከ በርካታ ደቂቃዎች ውስጥ ሊከሰት የሚችል የትንፋሽ መቆራረጥ ነው። ይህም በእንቅልፍ ልብ ውስጥ ሆኖ መተንፈስ ሲያቅት፥ ወይም ዝቅተኛ የሆነ አተነፋፈስ ሲከሰት ወይም ለተወሰኑ ሰኮንዶች ወደ ውስጥ እና ወደ ውጪ መተንፈስ አዳጋች ሲሆን ማለት ነው። ምናልባትም በአንድ ሰዓት ውስጥ ከ15 እስከ 30 ጊዜ እና ከዚያም ጊዜ በላይ ሊከሰት ይችላል። በእንቅልፍ ልብ መታፈን በዳይሶምኒያ (dyssomnia) ማለትም በእንቅልፍ ጊዜ ጤናማ ያልሆነ ባሕርይ ወይም የስነ ልቦና ችግር ሥር ሊካተት ይችላል። መተንፈስ ሲቆም ካርቦንዳይኦክሳይድ የደም ዝውውሩን ያቆማል። በዚህ ጊዜ አንጎል የተኛውን ሰው ከእንቅልፉ ተነስቶ አየር እንዲተነፍስ ምልክት ይሰጠዋል።

በእንቅልፍ ውስጥ መታፈን በአተነፋፈስ መቆራረጥ እና መቆም የሚከሰት ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል። ሦስት ዓይነት በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ዓይነቶች

• የሚያውክ በእንቅልፍ ልብ መታፈን (Obstructive sleep apnea)፦ብዙውን ጊዜ የጉሮሮ ጡንቻዎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የሚፈጠር የተለመደ መታፈን ዓይነት ነው።

• መካከለኛ የሆነ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ዓይነት (Central sleep apnea)፦ ይህ ዓይነቱ በእንቅልፍ ልብ መታፈን የሚመጣው አንጎላችን የአተነፋፈስ ሥርዓትን ለሚቆጣጠረው ጡንቻ ትክክለኛውን መረጃ ሳያስተላልፊ ሲቀር ነው።

• ውስብስብ የሆነ ወይም የተዘበራረቀ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ዓይነት (complex or mixed sleep apnea)፦ ይህ ዓይነቱ በእንቅልፍ ልብ መታፈን የመጀመሪያው እና የሁለተኛ የመታፈን ዓይነት ውህድ ነው።

ምክንያት (Cause)

ማንኛውም ሰው ማለትም ወንድ፥ ሴት፥ ወጣት፥ ጎልማሳ፥ ልጆች እና ሽማሌ ሳይቀር በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግር ሊገጥመው ይችላል። ይህ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግር የሚከሰተው ከጉሮሮ በስተጀርባ በኩል ያለው ጡንቻ በሚሳሳብበት ጊዜ ነው። ይህ ጡንቻ በሚሳሳብበት ጊዜ የአየር ማስተላለፊያው ቱቦ ይጠብና ወይም ይዘጋና ተገቢ የሆነ የአየር መጠን ወደ ውስጥ ለማስገባት እና ለማስወጣት አዳጋች ያደርገዋል። ይህ ደግሞ በደም ውስጥ መገኘት የሚገባውን የኦክሲጅን መጠን ይቀንሳል። ከዚህም የተነሳ በእንቅልፍ ልብ ውስጥ መታፈንን ሊያስከትል ይችላል።

ሌላው መካከለኛ የሆነው በእንቅልፍ ልብ የመታፈን (Central Sleep apnea) የችግር ዓይነት መነሻው አንጎል ምልክቶችን ለመተንፈሻ ማስተላለፍ ሲያቅተው የሚከሰት ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ረዘም ላለ ጊዜ መተኛት ወይም ፈጽሞውኑ እንቅልፍ እንዳይይዝ ሊያደርግ ይችላል።

ምልክቶቹ (symptoms)

በእንቅልፍ ልብ መታፈን የሚከሰተው አንድ ሰው ከተኛ በኋላ ስለሆነ ምልክቶቹን በራስ ማወቅ በጣም አስቸጋር ነው። ነገር ግን አብሮን የሚተኛ ሰው ካለ እርሱ/ሷን በመጠየቅ ወይም ስንተኛ የድምጽ መቅረጫ በአጠገባችን በማድረግ ምልክቶቹን ማወቅ ይቻላል። አንድ ሰው እያንኮራፋ እያለ ካቋረጠ እና የትንፋሽ መቋራረጥ እና መተናነቅ ከተከሰተ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግር እንዳለ የሚያሳይ ዋናው ምልክት ነው። ሌላው ቀን ላይ ጸጥ ባለ ጊዜ በሥራ ቦታ ይሁን አሊያም መኪና እያሽከረከሩ እንቅልፍ የሚጫጫኖት ከሆነ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል። ሌሎች ምልክቶች፦

• በማለዳ የሚከሰት የራስ ህመም

• ማስታወስ እና መማር ላይ ችግር ማስከትል ወይም ለአንድ ነገር ትኩረት ለመስጠት ሲሳነን

• የቁጡነት ስሜት መላበስ፥ መጫጫን እና የባሕርይ ለውጥ መታየት

• ለሽንት በተደጋጋም ከእንቅልፍ መንቃት

• ከእንቅልፍ ሲነቁ የአፍ መድረቅ ወይም የጉሮሮ ቁስለት ሲከስት ዋና ዋናዎቹ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ምልክቶች ናቸው።

ምርመራ  (Exams and Tests)

የጤና ባለሙያ የሚታየውን ምልክቶች መሠረት በማድረግ ምርመራ ካደረገ በኋላ የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው ሰዎች ህክምና በሚከታተሉበት ማዕከል እንዲተኙ ሊመክሮት ይችላል። እዚያም የእንቅልፍ ችግር ያለባቸውን የሚያክሙ የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች በሌሊት የአየር አተነፋፈስን እና በእንቅልፍ ውስጥ እያሉ ሌሎች የሰውነት ተግባራትን ሊገመግሙ ይችላል። እነዚህ ምርመራዎች ኖክቱርናል ፖልይሶምኖግራፊ (Nocturnal polysomnography) በተባለ መሣሪያ በመታገዝ የልብ ምርመራ፥ የሳንባ እና የአእምሮ እንቅስቃሴ፥ የአተነፋፈስ ሥርዓትን፥ የእጅ እና የእግር እንቅስቃሴን እና በእንቅልፍ ላይ እያሉ በደም ውስጥ የሚገኘውን የኦክሲጅን መጠንን የሚቆጣጠር የምርመራ ዓይነት ያካሄዳሉ። ሌላው ደግሞ በቤት ውስጥ በመኝታ ጊዜ የሚደረግ ምርመራ (home sleep test) የሚባለው ነው። ይህ የጤና ባለሙያ በሚሰጠው መመሪያ መሰረት በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ምልክቶችን ለማወቅ በግል የሚደረግ ምርመራ ነው። ይህም የልብ ምት ፍጥነት፥ በደም ውስጥ የሚገኝ የኦክስጂን መጠን፥ የአየር ምልልስ እና የአተነፋፈስ ሥርዓትን መለካት የሚጠይቅ ነው። ይህም ምርመራ የሚከናወነው ይህን ምርመራ ሊያደርግ በሚችል ተንቀሳቃሽና አነስተኛ በሆነ መሣሪያ አማካይነት ነው።

መከላከያው (Prevention)

በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግር በግል ጥንቃቄ በማድረግ መፍትሔ ማግኘት የሚቻል ችግር ነው። በእርግጥ በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግርን ለማቃለል ብዙ ሥራዎችን ማከናወን ይጠበቅብናል። በእንቅልፍ ልብ የመታፈን ችግርን ለመቅረፍ የአኗኗር ዘይቤን በመለወጥ እና የቤት ውስጥ እንክብካቤ በማድረግ ረጅም ሂደት ማድረግ ይጠይቃል። ለምሳሌ ግዙፍ የሆነ ክብደት ያላቸው ሰዎች ትርፍ የሆነ ጡንቻ በጉሮሮአቸው ላይ ስለሚኖር በሚተኙበት ጊዜ ያ ትርፍ የሆነው ጡንቻ የአየር ማስተላለፊያውን ቱቦ ሊዘጋው ይችላል። ስለዚህ የሰውነትን ክብደት መቆጣጠር ወይም መቀነስ አንዱ በቤት ውስጥ የምናደርገው የችግሩ መፍትሔ ነው።

ሌሎች ልናደርጋቸው የሚገቡ እንክብካቤዎች ስጋራ ማጨስን ማስወገድ፥ አልኮል መጠጦችን መጠጣት ማቆም፥ የእንቅልፍ መድኃኒት መውሰድን ማቋረጥ፥ ካፌን የተባሉትን አነቃቂ መጠጦችን እና ከበድ ያሉ ምግቦችን በማስወገድ፥ እና ቋሚ የሆነ የእንቅልፍ ጊዜ እንዲኖረን በማድረግ ችግሩን ማቃለል ይቻላል። ከዚህም በተጨማሪ በምንተኛበት ጊዜ በጎን በመተኛት፥ ከአንገታችን ቀና ብለን በመተኛት ወይም ትራስ በመጠቀም እና እንቅልፍ በምንተኛበት ጊዜ አፍንጫችንን ንጽህ በማድረግ በቀላሉ አየር ወደ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ችግሩን መቆጣጠር እንችላለን።

ህክምናውወይምመድኃንቱ ( Medication)

ችግሩን ለማቃለል በግል ማድረግ የሚገባን ነገሮች ማለትም የአኗኗር ዘይቤን በመለወጥ፥ እና እንክብካቤ አድርገንም እየባሰ ከሄደ ወደ ሐኪም ጋር መሄድ ይመከራል። የእንቅልፍ ችግርን የሚያክሙት ባለሙያዎች ምልክቶቹን ከተመለከቱና ከገመገሙ በኋላ ጠቃሚ የሆነ ሕክምና ሊሰጡ ይችላሉ። ውስብስብ እና መካከለኛ ለሆነ በእንቅልፍ ጊዜ መታፈን የሚሰጡ ህክምናዎች፦

• ይህን በእንቅልፍ ጊዜ የመታፈን ችግር የሚያስከትሉ የጤና ችግሮችን ማለትም እንደ ልብ ወይም የነርቭ ጡንቻ መዛባትን ማከም

• በእንቅልፍ ሰዓት ሰውነት ተጨማሪ ኦክስጂን የሚያገኝበትን ሁኔታ በማመቻቸት

• የዚህ አደገኛ የሆነው በእንቅልፍ ጊዜ መታፈን ችግርን የሚቆጣጠር መሣሪያ በመጠቀም ሊሆን ይችላል። የሚሰጡት መድኃኒቶች በሙሉ በእንቅልፍ ጊዜ ከመታፈን ጋር ተያይዘው የሚመጡትን የእንቅልፍ ማጣት ችግሮችን ለማከም ብቻ ይሰጣሉ።

ምንጭ:- ዋናው ጤና ድህረ ገፅ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.