Saturday, February 29, 2020
Home > ጤና > ስለ ስትሮክ ምን ያህል ያውቃሉ?

ስለ ስትሮክ ምን ያህል ያውቃሉ?

የደም መርጋት በሽታ በአንጎል ህዋስ መሞት ምክንያት በድንገት በኦክሲጂን እጥረት የሚከሰት በሽታ ነው። ከዚህም የተነሳ በዚህ በሽታ የተጠቃ ሰው በድንገት መናገር አለመቻል፥ የአእምሮ ችግር ወይም ሰውነቱ በአንድ በኩል ሽባ መሆን ይገጥመዋል። ሁለት አይነት የደም መርጋት በሽታዎች አሉ። እነርሱም ኢስኪሚክ እና ሄሞራጂክ የደም መርጋት በሽታ በመባል ይታወቃሉ። ኢስኪሚክ የተባለው ደም መርጋት በሽታ የሚከሰተው የረጋ ደም ወደ አንጎል ደርሶ ወደ አንጎል ደም እንዳይገባ ሲደፍነው ነው። ሄሞራጂክ የተባለው ደግሞ በአንጎል ላይ ያለው የደም ስር ሲተረተር ወይም ሲሰነጠቅ በአንጎልና በጭንቅላት መካከል ደም ሲፈስ የሚከሰት በሽታ ነው።

ምክንያት (Cause)

ኢስኪሚክ የተባለው የደም መርጋት በሽታ የሚከሰተው ትሮምቦስ ወይም ኢምብለስ የሚባለው ደም ወደ አንጎል እንዳይፈስ በመዘጋቱ ምክንያት የሚከስት በሽታ ነው። የደም መርጋት ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው አተሮስክሎሮሲስ በተባለው ወደ አንጎል ደም የሚያመጣውን በሚያጠቃው ጊዜ ነው። ይህ ደግሞ የልብ ምት ሥርዓቱን ጠብቆ እንዳይሄድ በማድረግ ቀሰ በቀስ ወደ ደም መርጋትና ደም ግፊት ይለወጣል። ሄሞራጂክ የተባለው የደም መርጋት በሽታን እንዲከሰት የሚያደርገው ምክንያት ክፈተኛ የደም ግፊትና ጭንቅላት ለአደጋ በመጋለጥ ወይም በአደጋ ምክንያት በመጎዳት ነው። የደም መርጋት አንዳንድ ጊዜ “የአንጎልና የደምስሩ ጥቃት” በመባል ሊታወቅ ይችላል። 80% የደም መርጋት በሽታ የሚከሰተው ኢስኪሚክ የተባለው በሽታ ነው። ይህም ደም ወደ አንጎል ውስጥ እንዳይገባ የሚያቋርጠው የበሽታ አይነት ነው። ሌላው 20% የበሽታው አይነት ሄሞራጂክ የሚባለው የደም መርጋት በሽታ አይነት ነው። ይህም የበሽታ አይነት በአንጎል ውስጥ የደም ሥሮች ሲዳከሙ የሚከሰት የበሽታ አይነት ነው።

ምልክቶቹ (symptoms)

የደም መርጋት ደም በአግባቡ ወደ አንጎል ውስጥ መፍሰስ አለመቻል ነው። የዚህ በሽታ ምልክቶችም በርካቶች ናቸው። የማየት ችግር ወይም የአይን መፍዘዝ፥ የመናገር ችግር ወይም ንግግር መደበላለቅ፥ ሽባነትን የሚያመጣ የጡንቻ ወይም የእግር መድከም፥ መደንዘዝ ወይም የሰውነት ሚዛንን መሳት ወይም መጠበቅ አለመቻል፥ በድንገት የሚከሰት የጡንቻ፥ የእግር፥ በአንድ በኩል የፊት ወይም የደረት ህመም፥ ድንገተኛ የሆነ አደገኛ የራስ ምታት፥በአንድ በኩል ያለው ፊት መድከም ወይም የፊት መጣል፥ ይበልጥ በሴቶች ላይ የሚታይ ድካም ወይም የአእምሮ መለወጥና ማቅለሽለሽ፥ የመተንፈስ ችግር ወይም ልብ የሚበር የሚመስል ስሜት መሰማት ጥቅቶቹ ናቸው።

ምርመራ (Exams and Tests)

የደም መርጋት በሽታ ምርመራ ሲደረግ ጊዜ በጣም ወሳኝ ነው። በፍጥነት ወደ ሀኪም ቤት መሄድ ለጤና ባለሙያው ወዲያውኑ ከበሽታው ለማገገም የሚያስችል መድኃኒት እንዲሰጥ ያስችለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ የሚደረገው ምርመራ የደም መርጋት በሽታው ኢስኪሚክ ወይም ሄሞራጂክ መሆኑን መለየት ነው። ለሁለቱም የደም መርጋት በሽታ አይነቶች የተለያዩ ህክምናዎች ስለሚያስፈልጋቸው ይህን መለየቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የጤና ባለሙያው በመጀመሪያ ደረጃ አንጎል መድማቱንና አለመድማቱን ሊያሳይ የሚችለውን ኮምፒውቲድ ቶሞግራፍ በሚባል መሣሪያ በመጠቀም ምርመራ ያደርጋል። የደም ሴል ቁጥር መጠንን (CBC)፥ በደም ውስጥ ያለ የስኳር መጠን፥ የጉብትና የኩላሊትን ሥራ ለማወቅ የደም ምርመራ ይደረጋል። የጤና ባለሙያው ከጠረጠረ ወይም ምርመራዎች ካሮቲድ አርተሪ የጠበበ መሆኑን ከጠቆሙ፥ በአርተሪ ውስጥ የደም ፍሰትን ለማረጋገጥ የካሮታይድ አልትራሳውን ሊታዘዝ ይችላል። የጤና ባሙያው በሽታው ምናልባት በልብ ችግር ምክንያት የተከሰተ መስሎት ከታየ የተለያዩ የልብ ምርመራዎች እንዲደረጉ ሊታዘዝ ይችላል።

መከላከያው (Prevention)

የደም መርጋት በሽታን ወደዚህ በሽታ የሚያመጡ ነገሮችን በማስወገድና ሌሎች ተያያዥ የጤና ሁኔታን በመከታተል ለመከላከል ይችላል። የደም በሽታን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች እንደ ማጨስ፥ ከፍተኛ የደም ግፊት፥ ከተገቢ በላይ የሆነ የኮሌስትሮል በሰውነት ውስጥ መገኘት፥ የስኳር በሽታ፥ ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት፥ ተከታታይነት ያለው የሰውነት እንቅስቃሴ አለማድረግና የአልኮል መጠጥ ማዘወተር ናቸው። ስለዚህ ይህን በሽታ ለመከላከል ማንኛውንም የጤና እክል ሲገጥመን ሕክምና መከታተል፥ ጤናማ የአኗኗር ዘዬን መከተል(አለማጨስ፥ ክብደትን መቆጣጠር፥ የተመጣጠነ አመጋገብ ስልት መከተል፥ አልኮል መጠጦችን አለማዘውተር፥ እና የልብ ምትን መከታተል ከመከላከያ መንገዶቹ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ህክምናው ወይም መድኃንቱ ( Medication)

የደም መርጋት በሽታ ከተከሰተ በኃላ የጤና ባለሙያው የተለያዩ መድኃኒቶችን ሊያዝ ይችላል። በሽታው በደም መርጋት ምክንያት የሚከሰቱ እንደመሆኑ መጠን የደም መርጋትን የሚከላከሉ መድኃኒቶች በብዛት ጥቅም ላይ ይውላሉ። የኮሌስትሮል መብዛትን የሚቀንሱና የደም ግፍትን የሚቀንሱ መድኃኒቶችም ይታዘዛሉ። እነዚህን ሁኔታ ለመቆጣጠር እንደ አስፒሪን፥ ክሎፒዶግሪል፥የካልሲየም መግቢያ የሚዘጉ፥ ጫናን እና ህመምን የሚቀንሱ መድኃኒቶች በሙሉ ለዚህ በሽታ ህክምና አገልግሎት ይሰጣሉ።

ዕሁፉን ያዘጋጀው፡ አለሙ ዘገየ ዲታ

ጽሁፉን የገመገመው የህክምና ባለሙያ: ዶ/ር ብሩክ ዘውዱ

የዕሁፉን ይዘት የገመገመው፡ አዲስ አለማየሁ ታዬ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.