Wednesday, April 1, 2020
Home > ዜና > ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበት የስኳር ፋብሪካተመረቀ!

ከ8 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበት የስኳር ፋብሪካተመረቀ!

FBC – የኦሞ ወንዝን በሚያዋስኑ በካፋና ቤንች ማጂ ዞኖች የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ ተመረቀ።

ፋብሪካውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ አህመድ የመረቁ ሲሆን፥ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና የኢፌዴሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ተገኝተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ፋብሪካውን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ኢትዮጵያ ታላላቅ የመሰረተ ልማቶቸን የመፈጸም አቅም እና ቁርጠኝነት እንዳላት ተናግረዋል።

ባለፉት 6 ወራት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን የተለየ አመራር በመስጠት ለመጨረስ በተገባው ቃል መሰረት ዛሬ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ ወደ ስራ ለመግባት የሚያስችለውን ዝግጅት በማጠናቀቁ በይፋ መመረቁን ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ አስመልክተውም ማንም የማራቶን ሩጫን መጀመር ይችላል ነገር ግን የመጨረኛውን የድል ወሰን እስኪደርስ ድረስ ጀማሪ ከመባል አይድንም፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችንን ልክ እንደ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 በድል የምንቋጭ መሆኑን እርግጠኛ ነኝ ብለዋል።

ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የስራ መስክ በተገቢው መንገድ ሀላፊነቱን ከተወጣ እንደኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ ሌሎችን ፕሮጀክቶችንም በታለመላቸው ጊዜና ወጪ ማጠናቀቀቅ እንደሚቻልም ነው የገለጹት።

በዚህም በኦሞ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክቶች ውስጥ ያለው የሰው ሃይል በአመዛኙ ወጣት ሲሆን፥ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች ታላላቅ ሀገራዊ ሃላፊነቶችን በምን ደረጃ መወጣት እንደሚቻል ትምህርት ሊወስዱበት የሚችል ነው ብለዋል።

ብርቅዬ የተፈጥሮ ግብዓቶቻችንን በመጠቀምእና ወጣቶችን በልማት በማሳተፍ ሰው ሀገር ሄደን የምናያቸውን ትልልቅ ነገሮችን ሀገራችን ውስጥ እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መኖራቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የተናገሩት።

በሌላ በኩል ደግሞ ትልቅ ስላሰብን ትልልቅ ስራዎችን ብቻችንን አንሰራም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከኤርትራ ጋር የወጠኘነውን የሰላም ለውጥ ተከትሎ የጋራ በሆኑ የልማት ተፋሰሶች ላይ ከኤርታራአውያን ወንድም ህዝቦች ጋር አብሮ የማደግ እቅድን በመወጠን የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ዛሬ የተመረቀው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የስኳር ፋብሪካ ድረስ መጋበዛቸው ነው የገለፁት።

በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለ መሪያም ደሳለኝ የተገኙ ሲሆን፥ በደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደርነት ዘመናቸው ይህንን ታላቅ ሜጋ ፕሮጀክት በማስተለም እንዲሁም በሌሎች የስራ ሃላፊነቶቻቸውም ላይ አፈፃፀሙን በመከታተል ዛሬ የድሉን ክር አብረው እንዲበጥሱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተጋብዘዋል።

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስር ከሚገነቡት አራት ስኳር ፋብሪካዎች አንዱ ነው፡፡

ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ የተገነባው ይህ ፋብሪካ በቀን ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ኩንታል ስኳር የማምረት አቅም እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፥ ጥሬ ስኳር፣ ነጭ ስኳር እና የተጣራ ስኳር ያመርታል ተብሏል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 ስኳር ፋብሪካ መመረቅ ስኳር የሚያመርቱት ፋብሪካዎችን ቁጥር ወደ ስምንት ያደርሰዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 3 የግንባታ ሥራው በይፋ የተጀመረው በመጋቢት ወር 2008 ዓመተ ምህረት ከቻይና ልማት ባንክ በተገኘ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ነው፡፡

ለአራቱም ስኳር ፋብሪካዎች የሚውል በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ ለማልማት በኦሞ ወንዝ ላይ የመስኖ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በጥቅሉ 30 ሺህ ሄክታር መሬት ውሃ ገብ ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 16 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ መተከሉን ከስኳር ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

እስከ አሁን በቋሚ፣ በኮንትራትና ጊዜያዊነት ከ110 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችና ዜጎች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ከ300 በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ ከመጋቢት 2009 ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ የሚታወስ ነው፡፡

በሶዶ ለማ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.