Friday, November 15, 2019
Home > ዜና > ይድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ::

ይድረስ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ::

ውድ ኢትዮጵያኖች ይህ መልክት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ይደርስ ዘንድ ሁላችሁም ሼር በማድረግ ተባበሩን::

ጉዳዩ ፡ ወንድሜን ካፒቴን ዩሐንስ ተስፋ’ን በቤተ-መንግስትዎ አስጠርተው እንዲያነጋግሩት ስለመጠየቅ፤

እጅግ በጣም የማከብርዎት የኢትዮጵያ መጻኢ ብሩህ ተስፋ ማርሽ ቀያሪ እና ጎልማሳው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠቅላይ ሚንስቴር እጅግ በጣም የተከበሩ እና የተወደዱ ዶ/ር ዓብይ አህመድ፤

እነሆ ለበርካታ ዓመታት የተተበተበውን የፖለቲካ ሴራ ከስራ ባለድረባዎችዎት ጋር በመሆን በጣጥሰው ለትውልዱ ህልም የሚመስል አስደማሚ ለውጥ እንድናይ ስላደረጉን ከልቤ ደግሜ ደጋግሜ ላመሰግንዎት እንዲሁም እረጅም እድሜ እና ጤና ሰጥቶዎት የሚመኙት አዲስ ዘመን በዓይንዎት እንዲያዩ እምኝለዎታለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፡- እርስዎም ከአንድ ትንሽዬ መንደር፣ ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ ወጥተው፣ በአካባቢው መልካም ስነ-ምግባር ታንጸው፣ በድሃ ሃገርዎት እገዛ እና በአካባቢው ማህበረሰብ በጎ ድጋፍ፣ በታላላቆች ምርቃት፣ እንዲሁም በእራስዎ የግል ጥረት የታላቅ ሃገር ታላቅ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን የቻሉ ታላቅ ሰው በመሆንዎ የአንድ ገጠር ቤተሰብ ልጁን አስተምሮ ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት የሚከፍለውን የከበረ ዋጋ ለእርስዎ አልነግርዎትም፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር፡

ካፒቴን ዩሐንስ ተስፋ በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ በደጀን ወረዳ ልዩ ስሙ አለቅታም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተወልዶ እንደማንኛውም የገጠር ልጅ ያደገ የአርሶ አደር ልጅ ይሁን እንጅ የአእምሮ ብስለቱ እና ክህሎቱ ግን እንደማንኛውም ልጅ ሳይሆን እሱ በተለዬ እጅግ የላቀ ነበር፡፡

የያኔው ብላቴና የዛሬው በማንነቱ ምክንያት የግፍ ገፈት ቀማሽ የሆነው ካፒቴን ዩሐንስ ተስፋ እና እኔ የተዋወቅነው በ1991ዓ.ም ሲሆን ወቅቱም እሱ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ከተማረበት ዋርካ አለቅታም የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት አጠናቆ የትኖራ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ወደ 7ተኛ ክፍል በተዘዋወረበት ጊዜ ነበር፡፡

ከዩሐንስ የትውልድ መንደር እስከ የትኖራ በግምት አስር ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን 7ተኛ እና 8ተኛ ክፍል ዩሐንስ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን በየእለቱ በእግሩ እየተመላለሰ በመማር በየዓመቱ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በየዓመቱ አንደኛ ደረጃ የሚወጣው እሱ ብቻ ነበር፡፡

ዩሐንስ 9ኛ እና 10ኛ ክፍል ትምህርቱን በደጀን ከተማ በሚገኘው ጎጃም በር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በመቀጠል እንደለመደው በከፍተኛ ውጤት ሁሉንም የትምህርት አይነት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ እና ካልተሳሳትኩ ስትሬት ፎር በማምጣት ቢቸና የሚገኘው የበላይ ዘለቀ የመሰናዶ ት/ቤትን ተቀላቀለ፡፡

በ 1995 እና በ 1996ዓ.ም ዩሐንስ በላይ ዘለቀ መሰናዶ ት/ቤት በ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ቆይታው ብዙዎቻችን የሶሻል ሳይንስ ስንመርጥ እሱ ግን የናቹራል ሳይንስን በመምረጥ እንደልማዱ ሁሉንም የትምህርት አይነቶች ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በ 1997 ዓ.ም መቀለ ዩንቨርሲቲ ገብቶ በ 2001ዓ.ም በኤሌክቲሪካል ኢንጂነሪንግ በከፍተኛ ውጤት ተመረቀ፡፡

ክቡር ሚንስትር ሆይ

ታዲያ ጉዳዩን ላሳጠረው ብዬ አሳጠርኩት እንጅ በተለይ ደጀን ጎጃም በር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለሁለት ዓመታት እና በላይ ዘለቀ የመሰናዶ ት/ቤትም እንዲሁ ለ ሁለት ዓመታት በድምሩ ለ አራት ዓመታት የተጠቀሱት ት/ቤቶች ከቤተሰቦቻችን ቀዬ ትንሽ ስለሚርቅ እና በየእለቱ ለመመላለስ አመቺ ስላልሆነ ዶርም በጋራ መከራየት ግዴታ ነበር፡፡

ይሄም ብቻ ሳይሆን እንደ ተማሪ በሳምንት አንድ ጊዜ ከቤተሰብ በሚላክልን ዳቦ፣ ቆሎ፣ በሶ፣ ድርቆሽ እና ጥቂት የኪስ ገንዘብ ነበር የትምህርት ጊዜያችን የምናሳልፈው፡፡

ይሄ ሁሉ ሲሆን አንዳንዴ የሚላክልን ምግብ ወይም ገንዘብ በዘገዬ ጊዜ ከጎጃም በር ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ወደ በላይ ዘለቀ መሰናዶ የመጣን ልጆች በብዛት የተከራዬነው ዶርም ቅርብ ለቅርብ ስለነበር ሲኖር ያለውን ተጋርተን፣ ሲጠፋ ዳቦ በውሃ ወይም ቆሎ ቆርጥመንም ቢሆን ሌሊቱን በጋራ ስናነብ እናድራለን ቀን ወደ ት/ቤት እንሄዳለን፡፡

በዚህ ሁሉ ጊዜ ዩሐንስ ሁሌም የምንኮራበት አብሮ አደግ፣ ጓደኛና የሚያስደምመን ትጉህ ተማሪ ሲሆን አንድም ጊዜ ውጤቱ ፍጹም ዝቅ ብሎ አያውቅም፡፡

ይህ ትጋቱም መቀለ ዩንቨርስቲ ቀጥሎ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በደ/ማርቆስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የቴክኒክ ት/ቤት ተመድቦ ለመስራት ከልጅነት ህልሙ ጋር ሳይጣጣም ሲቀር ደስተኛ ባለመሆኑ የትምህርት ማስረጃውን ይዞ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥቶ ስራ እየፈለገ ባለበት ሰዓት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎችን ለመቅጠር ያወጣውን ማስታዎቂያ ሰምቶ ተወዳደረ ፣ አለፈ፣ ሰለጠነ ተቀጠረ፡፡የልጅነት ህልሙ እውን ሆነ፤ ኢትዮጵያም የሚያገለግላት ወጣት ባለራዕይ ወጣት አብራሪ አገኘች፡፡

ይሁን እንጅ ከዩሐንስ የዓመታት አገልግሎት በኋላ የእግዚያብሔርን ዓይን በሚጠነቁሉ ባለጊዜዎች በግፍ ያላአግባብ ከሠማይ ወደ ምድር እንዲወርድ ተደርጎ፤ አብሮ አደጌ፣ የቀድሞ የክፍል አጋሬ፣ ጓደኛዬ፣ ወንድሜ ዩሐንስ ተስፋ ያ ሁሉ ውጣ ውረድ ከንቱ ሆኖ ተጎሳቁሎ፣ ከሰው ተራ ወጥቶ ግን ደግሞ አላጎበድድም፣ እምቢኝ ለባርነት አሻፈረኝ ብሎ አፈር ሲገፋ በአማራ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ ሳዬው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ያለውን ስርዓተ አልበኝነት አብዝቼ ኮነንኩት፡፡

ዩሐንስ ተስፋ በጣም ጭዋና የተረጋጋ ፖለቲካ ላይ ብዙ የማይንቀለቀል ግን ለሃገሩ መበልጸግ አብዝቶ የሚጨነቅ ብልህ ወጣት እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡

ብቻ በቀል የእግዚያብሔር ነው፤ አፈር ያስበሉት አፈር ይብሉ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚንስተር

እንግዲያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያዊያን ከሆነ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእኔም ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካፒቴን ዩሐንስ ተስፋም ነው፡፡

ስለዚህ በጋራ ሐብታችን የጋራ ፍትህ እንሻለን፡፡ ፍትህ ለተበደሉ፤ ወንጀለኞቹ ለፍርድ ይቅረቡ፡፡

ስለሆነም ለልጆቻቸው የተሻለ ነገ ሌት ከቀን የሚታትሩ ኢትዮጵያዊያን አባቶችን እና እናቶችን የሚያከብሩ ከሆነ እንዲሁም ለሐገራቸው ብዙ ራዕይ ሰንቀው ወገኖቻቸውን ለማገልገል ነገን የሚናፍቁ ታዳጊዎችን የሚያከብሩ ከሆነ፣ በጾለት እና በምርቃት ይህችን ሃገር ያቆዩንን የሐይማኖት አባቶች እና የሐገር ሽማግሌዎች የሚያከብሩ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን፣ የሃገሬን ምስኪን ማህበረሰብ የሚያከብሩ ከሆነ፤ የዜጎች በሃገራቸው ሰርቶ መለወጥን እና በሃገር መኩራትን የሚያከብሩ ከሆነ፣ ካፒቴን ዩሐንስ ተስፋን ማናገር ፤

ያላአግባብ የተገፉ ንጹሐን ኢትዮጵያዊያንን ማክበር ነውና ወንድሜን ካፒቴን ዩሐንስ ተስፋ’ን በቤተ-መንግስትዎ አስጠርተው እንዲያነጋግሩት በታላቅ አክብሮት እጠይቅዎታለሁ፡፡

አመሠግናለሁ!!!

እባካችሁ ይህ መልክት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ይደርስ ዘንድ ሁላችሁም ሼር በማድረግ ተባበሩን::

ምንጭ:-ጋዜጠኛ ማናዬ እውነቱ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.