Wednesday, April 1, 2020
Home > ዜና > ብጉር ምንድነው ? እንዴትስ መቀነስ ይቻላል?

ብጉር ምንድነው ? እንዴትስ መቀነስ ይቻላል?

ብጉር የቆዳ ችግር ሲሆን ዘይት/ቅባት እና የቆዳችን የሞቱ ሴሎች የቆዳ ቀዳዳዎችን በሚደፍኑበት ጊዜ ይፈጠራል። ጥቂት ቀያይ ነጠብጣቦች በቆዳዎ ላይ በሚኖሩበት ጊዜ ብጉር እየጀመርዎት ነው ማለት ነው።

ከባድ ብጉር የሚባለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ነጠብጣቦች(ጠቃጠቆ) በፊት፣ አንገት፣ ደረትና ጀርባዎ ላይ ሲከሰቱና እነዚህ ነጠብጣቦች ትልቅ፣ ደረቅና በጣም ህመም ያለው ቀይ እብጠት ሊሆን ይችላል። ብጉር በወጣትነት/ጉርምስና እድሜ ክልል ውስጥ ያሉትን በከፍተኛ ሁኔታ ያጠቃል። ከወጣትነት ዕድሜ በኋላ ይጠፋል/ይቀንሳል።

✔ብጉር እንዴት ይከሰታል?

የተለያየ የብጉር አይነቶች አሉ በጣም የተለመደው ግን በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚከሰተው ነው። ለአቅመ አዳም እና ሄዋን ስንደርስ የሆርሞናችን መጠን ይጨምራል በተለይ ቴስቴስትሮን። ይህ የሆርሞን ለውጥ የቆዳችን ዕጢ ብዙ ዘይት(ሴበም) እንዲያመርት ያደርገዋል። በቆዳችን ቀዳዳ የሚወጣው ዘይት ዋናው ጥቅሙ ቆዳችን ጤናማ ወዝ እንዲኖረው ማድረግ ነው። ብጉር የሚጀምረው ዘይት ከሞቱ የቆዳ ሴሎች ጋር ይቀላቀልና የቆዳችንን ቀዳዳ ይዘጉታል በዚህ ውህደት ውስጥ ባክቴሪያ ያገባና ያድጋል። ይህ ውህድ ከጐን ወዳለው የቆዳ ስጋ በማፈትለክ እብጠት፣ መቅላት እና መግል ይፈጥራል።

አንዳንድ መድሃኒቶች ለምሳሌ ኮርቲኮስቴሮይድ ወይም ሊቲየም ብጉሩ እንዲባባስ/እንዲያድግ ያደርጉታል። በብጉር የሚጠቁት ወጣቶች ብቻ አይደሉም አንዳንድ ጊዜ ገና የተለወደ ህፃን ብጉር ሊኖራቸው ይችላል ምክንያቱም ህፃናቶቹ ከመወለዳቸው በፊት የህፃኑ እናት ሆርሞን ወደ ህፃኑ ስለምታስተላልፍበት ነው።

አንዳንድ የኢንዶክራይን ስርዓት ችግሮች ለምሳሌ ፓሊሲስቲክ ኦቫሪያን ሲንድረም(polycystic ovary syndrome) እና ኩሺንግ ሲንድረም(Cushing syndrome) በብጉር እንድንወረር የሚያደርጉ በሽታዎች ናቸው።

✔በብጉር የመጠቃት እድልን የሚጨምሩ ሁኔታዎች:-

በብጉር ለመጠቃት የዘር ሀረግ ወይም ከቤተሰብ ጋር ይያያዛል ወላጅዎ ከባድ ብጉር ካለባቸው እርስዎም በብጉር የመያዝ እድልዎ ከፍተኛ ነው።

በብጉር የመጠቃት እድላችን ከፍ የሚለው በጉርምስና እና በመጀመሪያው የወጣትነት ዕድሜ ላይ ነው። የወር አበባ በሚታይበት ዕድሜ ክልል ላይ የምትገኝ ሴት በብጉር የመጠቃት ዕድል አላቸው። አብዛኛዎቹ ሴቶች የወር አበባ ከምትይበት ቀን በፊት ባሉት ቀኖች ላይ በጣም ትናንሽ የብጉር እባጮች ይኖራቸዋል።

የሚከተሉት ብጉርን የሚያባብሱ ሁኔታዎች ናቸው፦

※ ቆዳን የሚፈገፍጉ/የሚፈትጉ ነገሮች ለምሳሌ፦ ቀበቶ፣ ታይት፣ ሄልመንት፣ እጅ ላይ የሚታሰሩ ነገሮችና የመሳሰሉትን መጠቀም።

※ የፀጉርና ቆዳ መጠበቂያ ውጤቶች በተለይ በውስጣቸው የሞያሳክክ ንጥረ ነገር የያዙ

※ ፊትዎን ዘወትር/በተደጋጋሚ መታጠብ እና ፊትዎን ሲታጠቡ በጣም ማሸት።

※ ሸካራ ሳሙና መጠቀም እና በጣም የሞቀ ውሃ መጠቀም እንዲባባስ ያደርገዋል።

※ ጭንቀት ሲኖር

※ ፊትን በተደጋጋሚ መንካት

※ ላብ በብዛት ሲያልበን

※ በፊት ላይ በዛ ያለ ፀጉር መኖር የፊት ቆዳ ዘይት/ቅባት እንዲኖረው ያደርጋል።

※ አንዳንድ መድሃኒቶች መውሰድ(ኮርቲኮስቴሮይድ፣ ባርቢቱሬትስ ወይም ሊትየም)

※ በዘይት እና ኬሚካል ማምረቻዎች አካባቢ መስራት

※ አትሌቶችና ሰውነታቸውን የሚገነቡ ስፓርተኞች ስቴሮይድ ስለሚወስድ በብጉር የመጠቃት ዕድል አላቸው።

✔ የብጉር መከላከያ መንገዶች

ብጉርን መከላከል አይቻልም ነገር ግን እንዳይባባስ የሚወሰድ እርምጃዎችና ጥንቃቄዎች አሉ ከነዚህም መካከል፦

※ በዝግታ ወይም በጣም ሳይሹ መታጠብ ለቆዳዎ ጤንነት አስፈላጊ ነው። በጣም ማሸት፣ መጥረግ፣ መፈተግ ወይም መፈግፈግ ተገቢ አይደለም።

※ በጣም እንዳያልብዎ መጠንቀቅ። ላብ እንዲያልበን የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች ካደረግን በኋላ ወዲያው መታጠብ።

※ ፀጉርዎ ቅባት ካለው ወይም ከበዛበት መታጠብ።

※ አንዳንድ የፀጉር መንከባከቢያ ምርቶችን መጠቀም ማቆም ለምሳሌ፦ ጄል፣ ክሬምና የመሳሰሉት

※ ፊትዎን ቶሎ ቶሎ ከመንካት መቆጠብ

※ ለስላሳ የኮተን ልብሶችን መጠቀም በተለይ ከቆዳ ጋር ንክኪ ያላቸው።

※ ከቅባት እና ኬሚካል ጋር ያለዎትን ግንኙነት መቀነስ/ማቆም ለምሳሌ ፔትሮሊየም።

መልካም ጤንነት!!!

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.