Saturday, February 29, 2020
Home > ዜና > ይድረስ ለኢፌዴሪ መንግስት!

ይድረስ ለኢፌዴሪ መንግስት!

ጉዳዮ የመንግስት ባለስልጣናት #በፌስቡክ አጠቃቀም መስመር እንዲይዝ ስለመጠየቅ

በክልልም ሆነ በፌደራል መንግስት ስልጣን ላይ የሚገኙ አመራር አካላት እንደእኛ የፌስቡክ ብሽሽቅ ውስጥ ገብተው ሲንከራተቱ ማየት ለመንግስትም ለሚወክሉት ህዝብም አሳፋሪ ነው። ከዚህ ቀደም አሳፋሪ ነገሮችን ከፃፉ በኃላ አካውንታቸው ሃክ ተደርጎ ነው የሚል ሰበብ ሲሰጥ እንደነበር ይታወቃል።መንግስት በተፈጥሮው ለትችት የተጋለጠ እና የሁሉም ሰው ቁጣ የሚደርስበት ተቋም ነው። በመሆኑም ቁጣ በደረሰበት ቁጥር ዛቻ መሰል ንግግሮችን መፃፍ ከዚህ በፊት ያየነው ሲሆን አሁን ደሞ በክልል አመራር ደረጃ ያሉ ሰዎች ሳይቀር ለአንድ የማይረባ ፓርቲ ሃላፊ የማይረባ አርቲክል የብሽሽቅ መልስ ሲሰጡ ይታያል።

የኢፌዴሪ ፌደራልም ሆነ ክልላዊ መንግስት እንደሰለጠኑት አገራት የሶሻል ሚዲያ ፓሊሲ ባይኖረው እንኳን የመንግስትን አቋም የሚያጋሩን እንዲሁም በከፍተኛ የፓርቲ እና የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ የፓለቲካ ሹመኞች ከብሽሽቅ ፣ ከዛቻ እና እንካ ሰላምታ ርቀው ህዝብ ለህዝብ የሚያቀራርቡና በተደጋጋሚ የተሞገሱባቸው ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ።

አሁን በንፅፅር ተወዳጅ መንግስት እየመሩ እንዲህ ለትናንሽ ነገር ብሽሽቅ ውስጥ ከገቡ ለትልልቅ ተቃውሞዎችም ያላቸውን ዝግጁነት ያስጠይቃልና ቢታሰብበት መልካም ነው።

የመንግስት ባለስልጣናት እንደማንኛውም ሰው ንዴት እና የማይሰማሙባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ብረዳም በተለይ የመንግስትን ሃሳብም በሚያነሱባቸው አካውንቶች የግል ፓለቲካዊ ሃሳብና ብስጭታቸውን ማቅረብ መንግስትንም ፓርቲያቸውንም ለሚስአንደርስታንዲንግ ያጋልጣልና ቢታሰብበትና ቶሎ መፍትሄ ቢሰጠው ጥሩ ነው። የጥሩ አመራር አንዱ መገለጫ ሆደሰፊነት እና ከመንግስትም ሆነ ከፓርቲም ሆነ ከግል እምነት ፍፁም የተለየ ሃሳብ መኖሩን ማመንና ማለፍ ነው። በተግባርም ቢሆን የሚዲያ ምህዳሩ በሰፋ ቁጥር ለሚፃፉ ብዙ ነገሮች ከፍተኛ የመንግስት አባል መልስ ሰጥቶም ተበሻሽቆም አይቻልምና፣ ጥብቅ ዲሲፕሊን ይታሰብበት።

በሶልያና ሽመልስ

ታዛቢ ዜጋ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.