Monday, March 30, 2020
Home > ዜና > ስለ የልብ ድካም ምን ያህል ያውቃሉ?

ስለ የልብ ድካም ምን ያህል ያውቃሉ?

የልብ ድካም በሽታ ወይም ማዮካርድያል ኢንፍራክሽን (Myocardial Infraction) የተባለው በቋሚነት የልብ ጡንቻ ላይ ጉዳትን ያስከትላል። ይህም የልብ ጡንቻ ደም እንዳያገኝ በማድረግ ጡንቻዎቹ እንዳይሰሩ ያደርጋል። የልብ ጡንቻ በአግባቡ ለመስራት ባለማቋረጥ በኦክስጂን  የበለጸገ የደም አቅራቦት ይፈልጋል። ኮሮነር አርተሪ (Coronary Artery) የተባለው ደም ሥር ይህን አስፈላጊ የሆነውን ደም ለልብ ያቀርባል። ይህን ኮሮነር አርተሪ የተባለውን ደም ስር በሽታ ካጋጠመው ይጠብና ወደ ልብ ተገቢ መጠን ያለውን ደም እንዳይፈስ ያደርጋል። ይህን አርተሪ የተባለውን ደም ስር ችግር ሲገጥመው ደም በውስጡ ይረጋና ይህን ደም ስር ይዘጋዋል። በዚህ ጊዜ ልብ ከመጠን በላይ የኦክስጂን ፍላጎት ያድርበታል። በጥቅት ጊዜ ውስጥ የልብ ጡንቻዎች ይሞቱና በዘላቂነት ይጠፋሉ። ይህ ደግሞ የልብ ድካምን ያስከትላል። ይህ በሽታ አንዳንድ ጊዜ በእረፍት ላይ ወይም በሥራ ላይም ሆነን ሊከሰት ይችላል።  ልብ በድካም ከተመታ በኃላ የልብ ጡንቻዎቹን ለመፈወስ ስምንት ሳምንታት ጊዜ ብቻ ይፈጃል። ነገር ግን ጠባሳው ስለማይሳሳ ድግመኛ ለልብ ድካም የማጋለጡ እድል ከፍተኛ ነው።

የልብ ድካም የሚከሰተው ወደ ልብ ደምና ኦክሲጅን የሚያመጣው የደም ስር በድንገት ሲዘጋና የኦክሲጅን እጥረት ስገጥመው ነው። አብዛኛው የልብ ድካም የሚከሰተው ኮሮነሪ በሚባል የልብ በሽታ (Coronary Heart Disease) ነው። ይህ ኮሮነሪ የሚባለው የልብ በሽታ የሚከሰተው ፕላክ የሚባል እንደ ሻማ ያለ ነገር ኮሮነር አርተሪ በሚባለው ደም ሥር ውስጥ ሲያድግ ይህን ደምና ኦክሲጅን የሚያስተላልፈውን የደም ስር ይዘጋዋል። ይህ ፕላክ የተባለው ነገር የሚያድገው ከብዙ ዓመታት በኃላ ነው። ይህ ደም ሥር መዘጋቱ አተሮስክሌሮሲስ (Atherosclerosis) ይባላል። ይህ ስፍራ ቀስ በቀስ ይቆስልና ደም በኮሮነሪ አርተሪ ውስጥ እንዲረጋ ያደርጋል። የዚህ ደም መርጋት ደም በአግባቡ ወደ ልብ እንዳይፈስ ያደርጋል። በዚህ ጊዜ የልብ ጡንቻዎች መሞት ይጀምራሉ። ጤናማ የነበረው የልብ ክፍል ይጎዳል። በዚህ ጊዜ ለልብ ድካም በሽታ ያጋልጣል።

ሌላው የልብ በሽታ መነሻው በኮሮነር አርተሪ ውስጥ የሚከሰት ስፓዝም (Coronary Artery Spasm) የሚባል በሽታ ነው። ይህ በሽታ ደም በአርተሪ ውስጥ እንዳይጓዝ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት የሚከሰት የልብ ድካም በጣም አነስተኛ ነው። ይህ ስፓዝም በምን እንደሚከሰት ማወቅ አይቻልም። ሆኖም ግን፡

• ከአንዳንድ መድኃኒቶች እንደ ኮኬን ከመሳሰሉት፥

• ከስሜት መጨነቅ ወይም ከህመም፥

• በጣም ቀዝቃዛ ለሆነ አየር በመጋለጥ፥ እና

• ሲጋራ ከማጨስ ጋር ሊያያዝ ይችላል

የተለያዩ የልብ ድካም ምልክቶች አሉ። እነርሱም:

• የደረት አከባቢ ምቾት ማጣት ወይም ህመም፥

• ሀመሙ ከወገብ በላይ ያለው የሰውነት ክፍላችን ላይ ማለትም ትከሻ፥ ጡንቻችን፥ አንገታችን፥ ጀርባችን እና መንጋጋችን ወይም ጥርሳችን ላይ የህመም ስሜት መሰማት፥

• የልብ መቃጠል የሚመስል የሆድ ህመም፥

• በአግባቡ በሥርዓቱ መተንፈስ አለመቻል፥

• ያለምንም ምክንያት የስጋት ስሜት መሰማት፥

• የጭንቅላት መደንዘዝ ወይም ባዶነት መሰማት፥

• በቀዝቃዛ ቆዳ ላይ ሳይታሰብ በላብ መዘፈቅ፥

• ከሆድ ህመም መከሰት የተነሳ ማቅለሽለሽና ማስመለስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የልብ ድካም በሽታ ምልክቶች የተለያዩ ሊሆኑ ይችላል። አንዳንዶቹን ቀለል ያለ የልብ ምቾት ማጣት ሲገጥመው ሌሎችን ደግሞ ከባድ የሆነ የህመም ስሜት ይሰማቸዋል።

ወደ ህክምና ጣቢያ ከሄዱ በኃላ የጤና ባለሙያዎች የአተነፋፈስ ሥርዓትን፥ የደም ግፊትን፥ እና  የልብ ምትን ይለካሉ። ይህን በሽታ ለመለየት የጤና ባለሙያዎች የኤሌክትሮካርዲዮግራም (electrocardiogram) የተባለውን ምርመራና ጠቅላላ የሰውነት ምርመራ ያካሄዳሉ። የላብራቶሪ ምርመራ የሚያካሂዱት ሰዎች የልብ ህዋስ ሲሞት በደም ውስጥ የሚለቀቀውን ካርዲያክ ኤንዛዬምን ለማወቅ የደም ምርመራ ያካሄዳሉ። ይህ ህመም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ከሆነ ካርዲያክ ካቴተራይዘሽን የተባለው ህክምና ወይም ካርዲያክቫስኩላር የቀዶ ጥገና ህክምና ይታዘዛል። ይህም ህክምና ኮሮነሪ አርተሪ የተባለው የደም ባንቧ ለማከም ያገልግላል።

ለልብ ድካም ዋና ምክንያት የሆነውን ኮርነር አርተሪን በበሽታ እንዳይጠቃ በመጠበቅ ይህን በሽታ መከላከል ይቻላል። ይህንንም ለመከላከል ፡

• ማጨስን ማቆም፥

• በሰውነት ውስጥ ኮሌስትሮልንና የደም ግፊትን መቆጣጠር፥

• የሰውነት እንቅስቃሴ በማድረግ፥ እና

• የአመጋገብ ሥርዓትን ለልብ ጤናማ እንዲሆን በማድረግ የልብ ድካም በሽታን መከላከል ይቻላል።

ለዚህ ህመም የታዘዙትን መድኃኒቶች በሙሉ ያለ ጤና ባለሙያው ፈቃድ ማቋረጥ ተገቢ አይደለም። መድኃኒቱን በአግባቡ መውሰድ በልብ ህመም በሽታ ከሚገጥመው የልብ ህመም መትረፍ ይቻላል። በድንገተኛ ህመም በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል እየተወሰዱ ከሆነ፥

• ለህመም ማስታገሻ ሞርፊን (Morphine) የተባለውን መድኃኒት፥

• ለአተነፋፈስ ሥርዓት ኦክስጂን ቴራፒ (Oxygen Therapy) ፥

• አርተሪ እንዳይደፈን የሚያግዝ ናይትሮግላይስሪን የተባለ መድኃኒት (Nitroglycerin)፥

• የልብ ምትን ለመቀነስ ደግሞ ቤታብላከርስ የተባለው ሲሰጥ (Beta-Blockers)፥

ከዚህም በተጨማሪ

• አስፕሪን (Aspirin)፥

• ደም እንዳይረጋ የሚያደርጉ መድኃኒቶች (Anticoagulants)፥

• ትሮምቦላይቲክስ (Thromoblytics) የተባሉ የረጋን ደም የሚያፈርሱ መድሃኒቶች በአየቪ (IV) መልክ በቬይን ውስጥ መስጠት፥

እና ወደ ሆስፒታል ሲደርሱ የጤና ባለሙያው ከነዚህ በተጨማሪ ሌሎችንም መድኃኒቶች እንደ አስፈላጊነታቸው ለህመምተኛው ይሰጣል።

ምንጭ: ዋናው ጤና ድህረ ጉፅ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.