Saturday, February 29, 2020
Home > ዜና > የኢንጂነር ስመኘው አባት ዛሬ ስላሉበትና ቃል ስለገቡላቸው ሰዎች ተናገሩ

የኢንጂነር ስመኘው አባት ዛሬ ስላሉበትና ቃል ስለገቡላቸው ሰዎች ተናገሩ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አባት በተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፡፡
የአባ በቀለ ዓይናለም ወንድም የሆኑት አቶ ሰጡ ዓይናለም ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደተናገሩት የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለአባ በቀለ ድጋፍ እያደረጉላቸው ነው፡፡

አቶ ሰጡ እንዳሉትም ወ.ሮ ፍሬዓለም ሺባባው በሐዘኑ ወቅት ለቤተሰቡ ለትራንስፖርተና ለሌሎች ወጭዎች የሚሆን 50 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገው ነበር፡፡ ከመስከረም ወር ጀምሮ ደግሞ በየወሩ አራት ሺህ ብር ለመርዳት በስድስት ወር ክፍያ (24 ሺህ ብር) ጀምረዋል፡፡ ወሮ. ፍሬዓለም ለአባ በቀለ የሚያደርጉት ድጋፍ እስከ ሕይወት ዘመናቸው የሚቀጥል መሆኑንም ወንድማቸው ተናግረዋል፡፡

የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ደግሞ ለአባ በቀለ 200 ሺህ እና ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ ልጆች 600 ሺህ ብር ቃል በገባው መሠረት መለገሱን የአባ ስመኘው ወንድምና የኢንጂነር ስመኘው በቀለ አጎት አቶ ሰጡ ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲም ለአባ በቀለ ነፃ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ቃል በገባው መሠረት በየትኛውም ሆስፒታል ሄደው መታከም የሚችሉበት የነፃ ሕክምና የምሥክር ወረቀት ለአባ በቀለ መስጠቱን ወንድማቸው ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ.ቤት ባሉበት ቤት እንዲሠራላቸው ቦታ ለመስጠትና ለማስተባበር ገንዘብም ለመደገፍ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጅ የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ እስካሁን ቃሉን መፈጸም አለመቻሉን ለመረዳት ችለናል፡፡ የማክሰኝት ከተማ ነዋሪዎች 11 ሺህ ብር እንደሰበሰቡ በሐዘኑ ወቅት የተገለጸ ቢሆንም እስከ ዛሬ ድረስ ገንዘቡ ወደ አባ በቀለ የባንክ ሒሳብ አለመግባቱንና በእጃቸውም አለመሰጠቱን አቶ ሰጡ ነግረውናል፡፡Image may contain: 1 person, hat

በተጨማሪም ለአባ በቀለ በዓይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝቶ የተመለከተው ዘጋቢያችን አረጋግጧል፡፡ በዓይነት ከደረሷቸው ድጋፎች መካከልም አልጋ፣ ኩታ፣ ጋቢ፣ ወንበር ይገኙበታል፡፡ የመኖሪያ ቤታቸውም በተሰበሰበው ብር ከነበረበት ቆርቆሮ በቆርቆሮ በችፑድ እየታደሰ ነው፡፡

ወ.ሮ ሙቀቴ የተባሉት የአባ በቀለ ዓይናለም የረዥም ጊዜ ጎረቤታቸው በቋሚነት እንዲያግዟቸውም በየወሩ 500 ብር ደመወዝ በወሮ. ፍሬዓለም ሺባባው በኩል እየተከፈላቸው ነው፡፡

አባ በቀለ ድጋፍ እያደረጉላቸው ላሉ ሁሉ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ለሚፈልጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች አባ በቀለ ዓይናለም የባንክ የሒሳብ ቁጥራቸው እንዲገለጽ ፈልገዋል፡፡ ስለሆነም ድጋፍ ማድረግ የምትፈልጉ ሁሉ በሒሳብ ቁጥሮች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000254323277 እና ህብረት ባንክ ፋሲል ቅርንጫፍ 2030416173549018 በኩል መርዳት የምትችሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት መስከረም 14/2011 ዓ.ም ‹‹ልጄ ከሞተ ጀምሮ በሀዘንና ትካዜ ውስጥ ነኝ፤ የነፃ-ህክምና ድጋፍ ይደረግላቸው የሚል ብጣሽ ወረቀት ይፃፍልኝ::››

‹‹በሚዲያ እንደሚረዱኝ የገለጹ አካላት እስካሁን ምንም አላደረጉልኝም፡፡›› በሚል ርዕስ የሟች ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አባት- አባ በቀለ አይናለም መግለጻቸውን መዘገቡ ይታወሳል፡፡

አባ በቀለ ቃላቸውን የፈጸሙትንና እገዛ ያደረጉላቸውን በሙሉ አመስግነዋል፡፡ በተለይ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ካለሁበት መጥቶ ያለሁበትን የኑሮ ሁኔታ በመመልከት ድጋፍ እንዲደረግልኝ የሚመለከታቸውን አካላት አናግሮ መፍትሄ ስላሰጠኝ ምስጋናየ የላቀ ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዳግም ለክትትል ወደ ጎንደር ሸምበቂት አምርቶ ለአባ በቀለ ዓይናለም ቃል የተገባላቸው ድጋፍ እየተፈጸመ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ እና አብርሃም በዕውቀት

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.