Monday, March 30, 2020
Home > ዜና > ስድብ ከህግ አንፃር እንዴት ይታያል የሰደባችሁን መልሳችሁ ብትድቡትስ?

ስድብ ከህግ አንፃር እንዴት ይታያል የሰደባችሁን መልሳችሁ ብትድቡትስ?

የህግ ባለሞያ ኪዳኔ መካሻ

‘‘የምላስ ወለምታ በቅቤ አይታሽም!!’’ ይባላል ባለማስተዋል ሳት ብሎት የሰውን ክብር መንካት እንኩዋን በቀላሉ እንደማይመለስ ለመግለፅ። ስድብ ጥግብ ማለት ከፈለጋችሁ የትም አትሂዱ።

እዚሁ ድሬ ቲዩብ አንዱ ፅሁፍ ላይ የሆነ አስተያየት ስጡ ወይም ፃፉ። ለመጻፍ ቀርቶ ለማሰብ የሚከብዱ ፀያፍ ቃላት እንደ ጉድ ይዘንቡባችኋል።‘‘ይህ ሰው ለምን ሰደበኝ? በሀሳቤ ካልተስማማ መተቸት ያለበት ሀሳቤን አይደለም እንዴ?’’ ብላችሁ ብትጠይቁ መልስ የለም።

ይሄን ፅሁፍ አንብበህ ወደ ኮመንት ወረድ ስትል እራሱ ጉድለትን የሚያሳዩ፣ የሚያነጋግሩ፣ የሚያበረታቱ፣ የሚያርሙ ፣ የሚያዝናኑ መልካም አስተያየቶችና ጥያቄዎችን እንደምታየው ሁሉ ከተነሳው ጉዳይ ጋር የማይገናኙ ፍረጃዎችን እና ስድቦችንም በዝተው ታያለህ።ምናለ በለኝ።

አንዳንዶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በስድብ አንደኛ ሲሆኑብህ ‘‘ይሄ ነገር በባህልም፣ በሀይማኖትም፣ በሕግም ክልክልነቱ ቀረ እንዴ?!’’ ትላለህ። ስድብ ግን የተፈቀደ እስኪመስለን ቢጧጧፍም ወንጀል ነው።

በወንጀል ሕጋችን በአንቀፅ 615 ስር ሰድብና ማዋረድ በክብር ላይ ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መሀል አንዱ ሆኖ ተደንግጓል።ማንም ሰው ተበዳዩን በቀጥታ በመናገር፣ በአሽሙር ስድብ ክብሩን ከነካ፣ በምልክት ወይም በሌላ በማናቸውም ሁኔታ ካዋረደ ተበዳዩ ክስ ካቀረበበት ይቀጣል።

ቅጣቱ ከሶስት ወር ማይበልጥ እስራት ወይም እስከ ሶስት መቶ ብር ሚደርስ የገንዘብ ቅጣት ነው።

ተሳዳቢዎችን በሶስት ብንከፍላቸውስ?

– የመጀመሪያው ተራ ተሳዳቢ ነው። እንዲያው ልማድ ሆኖበት አፉን የሚበላው ያገኘውን ሁሉ የሚሳደብ፣ ሚሰድበው ቢያጣ እራሱን ወይም እንሰሳትን ግኡዝ ነገሮችን ሁሉ የሚዘልፍ የስድብ ሱሰኛ ነው ፣

– ሁለተኛው ሰድቦ ለሰዳቢ የሚሰጥህ ነው። በአደባባይ ሰው እስኪሰማ ጠብቆ ተሳድቦ እንድትሰደብ ለቢጤዎቹ የሚጋብዝህ ወይም ‘‘ልክ ልኩን ነገርኩት፣ ሙልጭ አደረኩት፣እስኪበቃው አስታጠኩት!’’ እያለ የሰደበህንም ስድቦች በየአጋጣሚው እያወራ የሚነዛ ነው፣

– ሶስተኛው ተሳድቦ አሳዳቢ ነው። የፈለገ ጨዋ ብትሆን ደህና አድርጎ ሲዘረጥጥህ ወይም የሆነ አስፀያፊ ነገር ሲያደርግብህ ያለመሳደብ ትህትናህ ተንዶ አንተም እንድትሞልጨው የሚያስገድድህ ነው ። የስድብ ሙያ ምዘና ቢኖር ተሸላሚ ተሳዳቢ የሚሆን አይነት ሰው ነው።

በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጥናቸው ሰድቦ አሳዳቢዎችን ሕጉም ያውቃቸዋል።እነዚህ ተሳዳቢዎች አይደለንም ባንተ ላይ ሌላ ሰው ላይ ሲሆን የሚቀፍ እጅግ አሳፋሪ፣አስፀያፊ ወይም አስቀያሚ ትችት ሊሆን በሚችል ተግባር ቀስቅሰውህ ወይም ገፋፍተውህ ብትሳደብና ብትከሰስ በወንጀል ህጉ አንቀፅ 616 መሰረት ፍርድ ቤቱ ላይቀጣህ ይችላል።

በተለይ ምላሽህ ወዲያውኑ እና ከተሰደብከው ስድብ ጋር ተመጣጣኝ ከሆነ ሁለታችሁንም ወይም አንደኛችሁን ከቅጣት ነፃ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ምክንያቱም እነዚህ አይነትን ተሳዳቢዎች ችሎ ማለፍ እንደሚከብድ ሕጉ እራሱ ተረድቶታል።

በስድብ ተከሰህ ጉዳዩ እየታየ እያለ ያለአግባብ ነው የተሳደብኩት ‘‘ምነው ምላሴን ያን ቀን በቆረጠው!’’ በሚል ስሜት መጸጸትህን ከገለፅክም ፍ/ቤቱ ቅጣቱን ሊያቀልልህ ይችላል።

ከሳሽህን በሽማግሌ ይቅርታ ጠይቀህ ‘‘አፉ ብዬሀለሁ!’’ ካለህም በእርቅ ክሱ እንዲቋረጥ ማድረግ ትችላለህ።ስድቡ ቀላል ነው የሚባል ስድብ ወይም ማወረድ ከሆነ፣ነገሩ ተሰዳቢው እራሱ ካልገባው፣ ስድቡ ካልተሰራጨ ወይም ከሰዳቢና ከተሰዳቢ ውጭ ሌላ ሰው ካልተረዳው ቅጣቱም እንደ ስድቡና እንደ አሰዳደቡ ቀላል ነው።

ይህ አይነት ስድብ በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 844 ስር የደንብ መተላለፍ ጥፋት በመሆኑ እስከ መቶ ብር የገንዘብ ቅጣት ወይም በስምንት ቀን የማረፊያ ቤት እስር ልትቀጣ ትችላለህ። የተሳደብከው ግዴታውን በማከናወን ላይ ያለን የመንግስት ሰራተኛን ከሆነ ወይም ከመንግስት ስራው ወይንም ተግባሩ ጋር በተያያዘ መንገድ አስበህበት ከሆነ በአንፃራዊነት ቅጣቱ ከባድ ነው ከስድስት ወር ማይበልጥ እስርና ከአንድ ሺህ ብር ማይበልጥ መቀጮ ነው።

–የሀገራችንን መንግስት በአደባባይ መስደብ፣ ማዋረድ፣

– የፌደራሉን ወይም የክልል ሰንደቅ አላማዎችን በተንኮል ወይም በንቀት ወይም በመሰል ማንኛውም ሀሳቦች ተነስቶ መስደብ፣ መድፈር ወይም ማዋረድ በወንጀል ሕጋችን አንቀፅ 244 እንደተደነገገው ከሶስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ወይም በገንዘብ መቀጮ ያስቀጣል።

– የውጭ ሀገር መንግስትን ወይም መሪ፣– በሀገራችን የሚገኘውን የውጭ ሀገር የዲፕሎማቲክ አባል ወይም ተጠሪ መስደብ፣ ማወረድ ፣

–ከኢትዮጵያ ጋር ሰላማዊ ወዳጅነት ያለውን መንግስት የሉአላዊነት ምልክቶች በተለይም የዚሁ ሀገር ተጠሪ የሚያውለበልበውን አርማ ወይም ሰንደቅ አላማ፣

–በመንግስታት መሀል የተቋቋሙ እና ሀገራችን አባል የሆነችባቸውን ድርጅቶች ወኪል ወይም የታወቀ ምልክቱን ባደባባይ ማዋረድ በቀላል እስር ወይም በመቀጮ ያስቀጣል።

ሆኖም ክሱ የሚቀርበው የተሰደበው ሀገርም ተመሳሳይ ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆንና የሀገሪቱ መንግስት ተሳዳቢው እንዲከሰስ ጠይቆ የፍትህ ሚኒስትሩ ሲፈቅዱ ብቻ ነው ። ‘‘ቢቆስልም ይድናል የተደበደበ ስድብ ግን ይኖራል እንዳንገበገበ!!’’ እንዳለው ስሙ ያልታወቀ ገጣሚ ስድብ አነሰም በዛ ማስከፋቱ አይቀርም።

ስለዚህ ሀሳብ የመግለፅ ነፃነታችንን ስንጠቀም ስሜታዊ ባንሆን እና ሳብሳደብ ሀሳብን በሀሳብ በጨዋ ቃላት ብንተች ወይም ብንቃወም የተሻለ ነው። ሕጉን ብቻ ፈርተን ሳይሆን የራሳችንንም ህሊና አክብረን ባለ መሳደብ ለሌሎችም አርአያ በመሆን ጨዋነትን እናሳይ!!

ምንጭ ድሬ ቲዎብ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.