Saturday, February 29, 2020
Home > ዜና > “እናንተ ፍርዱኝ” በጣም አሳዛኝ እውነተኛ ታሪክ!

“እናንተ ፍርዱኝ” በጣም አሳዛኝ እውነተኛ ታሪክ!

ባለትዳር እና የሁለት ሴት ልጆች እናት ነኝ አንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሬ እሰራለሁ ከዛች ክፉ ምሽት በፊት በትዳሬ በልጆቼ ባጠቃላይ በኑሮዬ እንደኔ ደስተኛ ሰው አልነበረም።

ያንን ቀን እንደ ሁልግዜው በስራ ገብታዬ ነበር ያሳለፍኩት ሆኖም አመሻሽ ላይ መጨረስ የሚኖርብኝ ስራ ስለነበር በመደበኛ ሰዓቴ አልወጣሁም።

ለባለቤቴም ትንሽ ማምሸቴ ስለማይቀር በጊዜ ልጆቹ ጋር እንዲገባ ደውዬ ነግሬው ወደ ስራዬ ተመለስኩ ከምሽቱ 3:40 ስራዬን አጠናቅቄ ከቢሮዬ ወጣሁ በዛን ሰዓት ሚኒባስ ታክሲ ማግኘት የማይታሰብ ስለነበር የኮንትራት ታክሲዎች ከተደረደሩበት ስፍራ ደርሼ በወቅቱ ከነበሩት ሹፌሮች እድሜው በ40ዎቹ አጋማሽ የሚገመት ጎልማሳ መርጬ ወደሰፈሬ ለማድረስ የጠየቀኝን ሂሳብ ምንም ሳልከራከር ተስማምቼ ገባሁ:: ላዳዋ ግን ከፊትም ከኃላም ታርጋ አልነበራትም :: ግራ ገብቶኝ ስጠይቀው አሁሁን ነው ትራፊኮች የፈቱብን አለኝ:: እኔም ብዙ ሳልጨነቅ ጉዞ ጀመርን። የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ስላማረረን እኔና ባለቤቴ ከከተማ ትንሽ ወጣ ያለ ቦታ ቡራዩ አከባቢ መሬት ገዝተን ቤት ሰርተን ከገባን ገና አመት አልሆነንም ነበር።

ሹፌሩ በማላውቀው ወይም ባልለመድኩት መስመር ላዳዋን አዙሮ ሲነዳ ግራ ተጋብቼ

የኔ ወንድም ወዴት ነው የምትወስደኝ ስለው አይ በዚ በኩል አቋራጭ መንገድ አለ ይቀርበናል ብዬ ነው አለኝ:: እኔም በጣም ስለመሸ ምናልባት እንዳለውም ቶሎ ያደርሰን ይሆናል ብዬ ዝም አልኩ:: ጥቂት ከተጓዝን በኃላ የመብራት ብርሃን እንኳን በሌለበት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በድንገት መኪናዋን አቆማት ምነው ምን ሆንክ? አልኩት ደንግጬ…

እኔንጃ መኪናዋ ተበላሽታ ነው መሰለኝ ቆይ ወርጄ ከኃላ ልያት አለኝና ወርዶ የኃላውን ኮፈን ከፈተው:: ብዙም ሳይቆይ እኔ የነበርኩበትን የኃላ በር ከፍቶ

ይቅርታ ከጎንሽ የእጅ ባትሪ አለ አቀብይኝ አለኝ:: ግራ ተጋብቼ የቱጋ ነው ብዬ ወደጎኔ ስዞር አንገቴ ስር የሽጉጥ አፈሙዝ ደቀነብኝ::

አንዲት ነገር እተነፍሳለው እጮሃለው ብትይ በአንዲት ጣቴ ብቻ ምላጯን ስቤ እስከዘላለሙ አሰናብትሻለው። አለኝ

ወንድሜ ገንዘብ ከፈለክ ቦርሳዬ ውስጥ ያለውን ሁሉ ውሰድ እያልኩ ተንተባተብኩ::

ገንዘብሽን ሳይሆን ገላሽን ነው የምፈልገው አሁን አንድ በአንድ የለበስሽውን አውልቂ አለኝ:: ለመንኩት እባክህ የሁለት ልጆች እናት ነኝ እባክህ ባለትዳር ነኝ አልኩት:: ግን አልተሳካልኝም:: ሽጉጡን ወደኔ እያቀረበው በሄደ ቁጥር ነፍሴ ተጨነቀች ልጆቼ በአይምሮዬ ውስጥ ተመላለሱ እንባ ሳይሆን ደም እያነባሁ ያለኝን ነገር ሁሉ ፈፀምኩ::

የተመኘውን ገላ እንደልቡ ተጫውቶበት ሲያበቃ

ለፖሊስ እጠቁማለው ለሰው አወራለው ብትይ እጨርስሻለው አለኝ:: እራሴን ለማረጋጋት ሞከርኩና ህመሜን ስብራቴን ዋጥ አድርጌ ውይ ምን ችግር አለው በፊትም እኮ ሳታስገድደኝ እንዲሁ ብትጠይቀኝ እንስማማ ነበር ሽጉጡን ስላየሁ ነው እንጂ የደነገጥኩት አልኩት:: ምንም ችግር አልነበረውም ባይሆን ስልክ ቁጥርህን ስጠኝና ሌላ ጊዜ ተደዋውለን በሰፊው አሪፍ ጊዜ እናሳልፋለን አልኩት። ከት ብሎ ሳቀና ባንቺ ቤት አሁን ምንም የማላውቅ ፋራ አርገሽኛል አለኝ እኔም ያለ የሌለ መሀላ እየደረደርኩ ላሳምነው ሞከርኩ::

በመጨረሻም ያንቺን ስልክ ቁጥር ስጪኝና እኔ ደስ ባለኝ ቀን እደውልልሻለው አለኝ ሰጠሁት ከዛም ወደ ቤቴ አድርሶኝ ልክ ምንም እንዳልተፈጠረ እየሳኩኝ ደስተኛ መስዬ አመስግኜው ተለየሁት::

እቤት ስደርስ ቁጭ ብሎ የሚጠብቀኝ ባለቤቴ ላይ ተጠምጥሜ እያለቀስኩ ያጋጠመኝን ሁሉ ነገርኩት ድንጋጤ ድንዝዝ ቢያደርገውም እኔ እንድረጋጋ ብቻ አቅፎ ሲያባብለኝ ቆየና ጠዋት ለፖሊስ እንደምናመለክት ነግሮኝ አደርን::

በንጋታው ወደ ሆስፒታል ሄጄ ሙሉ ምርመራ አድርጌ ኤች አይ ቪ ለመመርመር ከ3 ወር በኃላ ደግሜ እንድመጣ ነግረውኝ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሄደን ካመለከትን በኃላ ወንጀለኛውን ለመያዝ ብቸኛው አማራጭ ያን ቀን ስልኬን ስለሰጠሁት እስኪደውል ብቻ መጠበቅ ነበርና ከ1 ሳምንት በኃላ ቅዳሜ ቀን የማላውቀው ቁጥር ተደወለ ሳነሳው እሱ ነው ምንም እንዳልተፈጠረ እንባዬን ወደ ውስጤ እየመለስኩ በሰላም አወራሁት ድምፁንም እየቀዳሁት ነበር:: ሰሞኑን ሁኔታዎችን አመቻችቶ እንደምንገናኝ ነገረኝና ዘጋው እሄን ለፖሊስ አመልክቼ በቀጣይ እስኪደውል መጠባበቅ ጀመርኩ::

ከ3 ቀን በኃላ በሌላ ስልክ ቁጥር ደወለ:: አሁንም ሰላም ብሎኝ ዘጋው በንጋታው በሌላ ስልክ ቁጥር ደወለ:: አሁንም አናግሮኝ ዘጋ:: በ4ኛው ላይ ልክ መጀመርያ ቀን በደወለበት ስልክ ደግሞ ደወለ:: ሰሞኑን እንደምንገናኝ ነገረኝ:: ፖሊሶችም ድጋሜ የደወለበትን ስልክ ይዘው የታክሲ ደንበኛ በመምሰል ደወሉለትና ለስራ እንደሚፈልጉት ነግረው ያዙት:: እኔም ተጠርቼ ሄድኩኝ ሳየው እራሱ ነው ዘልዬ ላንቀው ስል አጠገቤ የነበረው ፖሊስ ያዘኝ:: የክስ መዝገብ ተከፍቶ ምርመራ ተደርጎበት ሰውዬው ከዚ በፊትም ብዙ የወንጀል ሪከርድ እንደነበረበት ታውቆ የ16 አመት እስራት ተፈረደበት።

እኔ ከ 3 ወር በኃላ ሀኪም ቤት ሄጄ ኤች አይ ቪ ስመረመር በደሜ ውስጥ ቫይረሱ እንዳለ ተነገረኝ።

ዛሬ ፈጣሪና ውዱ ባለቤቴ ከጎኔ ባይኖሩ ኖሮ በህይወት አልኖርም ነበር እራሴን ለማጥፋት ስሞክር ስንቴ ከሞት አፋፍ ተርፌያለሁ ::

ቆይቼ ሳስበው ግን ቢያንስ ለልጆቼና በቫይረስ መያዜን እንኳን እያወቀ እስከዛሬ ከጎኔ ላልተለየኝ ባለቤቴ ስል መኖር እንዳለብኝ ገብቶኛል። ግን ሁሌም እፈራለው ምክንያቱም ሴት ልጆች ወልጃለው:: የኔ እጣ እንዳይደርሳቸው ሁሌም እፈራለው ከትምህርት እስኪ ገቡ እንኳን ልቤ አይረጋጋም:: እንደ እስረኛ ከግቢ አላሶጣቸውም:: ሱቅ እቃ እንዲገዙ እንኳን አልካቸውም።

ይህ ሁሉ ከሆነ 7 አመት አልፎታል:: እኔ ግን ዛሬም ህመምተኛ ነኝ ልቤ ተሰብሯል:: ፈሪ ነኝ ትንሽ ነገር ያስደነግጠኛል እራሴን አሞኝ ከተኛሁ በዛው ሞቼ የምቀር ይመስለኛል:: ልጆቼ የኔ እጣ እንዳይደርሳቸው ያስጨንቁኛል:: እኔን ብሎ ብዙ የተጎዳው ባለቤቴ ያሳዝነኛል።

በኔ የደርሰው በናተ ላይ አይድርስ:: የናተ አስተያየት ለኔ ስለሚጠቅመኝ ጥሩም ይሁን መጥፎ የተሰማችሁን ሀሳብ አጋሩኝ:: አስተያየታችሁን አንድ ባንድ አነባለሁ::

አመሰግናለሁ::

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.