Wednesday, April 8, 2020
Home > ዜና > ዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ችግር ላይ ነው!

ዛሚ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ችግር ላይ ነው!

በሃገር ውስጥ ቀዳሚ ከሆኑት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች መካከል አንዱ የሆነው ዛሚ 90.7 በችግር ውስጥ እንደሆነና ሊዘጋ እንደሚችል በስፋት እየተወራ ነው። በዚህና ጣቢያውን በሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ዘሪሁን ተሾመን ቢቢሲ አማርኛው አነጋግሯቸዋል፡፡

(ከዚህ በታች የቀረበው ቃለ ምልልስ በቢቢሲ ገፅ ላይ የቀረበ ነው፡፡)

የፋይናንስ ችግር አጋጥሟችኋል እየተባለ ነው

ምን እኛ ብቻ ነን እንዴ፤ አገርም ችግር አጋጥሟታል እኮ!

እንዴት?

ኢንደስትሪያል ፓርኩም ኢንቨስተር ካልተገኘ ቆርቆሮ ነው አይደለም እንዴ? የአገር ኢኮኖሚው ቀዝቅዟል። የአገር ኢኮኖሚ ከቀዘቀዘ የአንዳንድ ሴክተሮችም ኢኮኖሚ ይቀዘቅዛል። ሁለተኛው በየትኛውም የቢዝነስ [ሽክርክሪት] ውስጥ እኛ አገር ብርቅ ሆኖ ነው እንጂ መነሳት፣ መውደቅ፣ መሞት፣ እንደ አዲስ መፈጠር ያለ ነው።

ስለዚህ ችግር አጋጥሞናል እያሉኝ ነው፣ አቶ ዘሪሁን?

ቆየኝ…ቆየኝ! እነዚህ የተባሉት ነገሮች ሁሉ እውነት ናቸው ቢባሉ ሊገርም አያስችልም፤ ግን እንደዜና ሊቀርብ ይችላል። የሚገርም ነገር እና ዜና የሚሆን ነገር ይለያያል። ስለዚህ ቢቢሲም የሚገርም ዜና ብሎ ሳይሆን ምናልባት የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተለያዩ ሴክተሮችን ‘አፌክት’ እያረገ ነው በሚል ሊቀርብ ይችላል።

ስለዛሚ ሬዲዮ ትኩረት አድርገን እናውራ፣ አቶ ዘሪሁን?

ልመጣልህ ነው! ስለዛሚ እናውራ ከተባለ ዛሚ በሠራተኛ ደረጃ የዘገየ ደመውዝ የለም። የዘገየ ደሞዝ ቢኖር የዚህኛው ወር፣ እሱም የዘገየው ሁለት ቀን ነው። ስለዚህም ሁልጊዜ ወር በገባ በ30 እንከፍላለን። የአሁኑ ወር ላይ ወር በገባ በ30 ሳይሆን በ2 እና በ3 ተከፈለ። ምክንያቱም ደመወዝ የምንከፍለው ከምናገኘው የማስታወቂያ ገቢ ነው። ከምናገኘው የማስታወቂያ ገቢ የምንሰበስበው ደግሞ ማስታወቂያ [አምጪዎች] ሲከፍሉን ነው። እሱን በጊዜው ሊከፍሉን አልቻሉም። ደንበኞቻችን ናቸው። ስለሆነም እነሱን መጠበቅ ነበረብን። ያም ሆኖ ግን ተወጥተናል።

በአጋርነት በጣቢያችሁ የሚሠሩትም እየሸሹ ነው

የሄደው ኢትዯፒካሊንክ ነው። 6 ዓመት እኛ ጋር ቆይቷል። የራሱ ሬዲዮ ለመጀመር አሳብ አለው። እስከዛ ድረስ ለመሟሟቅ ወደ ፋና ሄጃለሁ ብሏል። ይሄምርጫቸውን እኛ ልናቆመው አንችልም።

ማስታወቂያ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ የገቢ ማነስ ሊሆን ይችላል፤ ቁጭ ብላችሁ ተነጋግራችኋል?

አውርተናል። በቃ ልንሄድ ነው ምናምን ብለው ነግረውኛል። ከፋና ጋር በፊት ባለመግባባት ነው የተለያዩት። አሁን የይቅርታና የመደመር ዘመን ስለሆነ ይቅርታና መደመር አግኝተው ሄደው ሊሆን ይችላል። (ሳቅ) እሱም የኔ ችግር አይደለም። ምርጫቸውን ግን አከብራለሁ፡፡ ወዳጆቼ ናቸው።

የ”ዛሚ ክብ ጠረጴዛ”…”ቆይታ ከሚሚ ስብሐቱ ጋ” ተቋርጧል እየተባለ ነው።

የ”ዛሚ ክብ ጠሬጴዛ” መቼ ነው የተቋረጠው የሚለውን እናንተ ፈትሹ።

አልተቋረጠም ነው የሚሉኝ፣ አቶ ዘሪሁን?

አልተቋረጠም ሳይሆን ላስረዳህ። የ “ቆይታ ከሚሚ ስብሐቱ” ፕሮግራም ሚሚ አገር ውስጥ የለችም፤ ወደ ውጭ ሄዳለች። ለምን ሄደች? ለግል ጉዳይ ሄደች። የግል ጉዳይዋ ምንን ይመለከታል? ራሷን ማስደሰት ሊሆን ይችላል፤ መታከም ሊሆን ይችላል መብቷ ነው። አንደኛው ይሄ ነው ይሄም ከሆነ በኋላ እሱን ለመተካት ሞክረናል። የሞከርነው ቤት ውስጥ ባሉ ጋዜጠኞች ነው። ስለሆነም አንድ ሳምንት ይቀርባል፤ አንድ ሳምንት አይቀርብም። እንደዚህ እያለ ሄዷል። በአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ ሁሉ ነገር ቢቀጥል በጣም አሪፍ ነው ቢቻል። እረፍት ሲወጡ የሚተካቸውና የእነሱን ካሊበር [ቁመና] የሚመጥን ሰው ቢኖር ሳይቋረጥ ቢሄድ አሪፍ ነው።ይሄ [ክስተት] የተገጣጠመበት ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቶ ነበር። አቧራ በአቧራ ነው። ማጨብጨብ ነው። ወዴት ነው የምንሄደው? እንዴት ነው የምንሄደው? ከጥቅል ነገሮች ውጭ ምንም ነገር የለንም። ስለሆነም በእንደዚያ ዓይነት ፕሮግራሞች ላይ የሚቀርብ ቀጥተኛ ንግግሮች፣ ዜጋ የሚሳተፍበት መድረክ ነው የሚሚ ፕሮግራም። ማንም የፈለገውን የሚያወራበት ላይቭ ነው። “ዊ ዲዲንት ዎንት ቱ ቴክ ዘ ሪስክ” [ኃላፊነት መውሰድአልፈለግንም]።

በአንድ በኩል ለውጥ አለ ብሎ ተስፋ ያደረገውን ኅብረተሰብም እና ለውጥ አለ ብሎ ያመነውንም የዚህች አገር ገዢ መደብ ምንድነው ለውጡ ብሎ ግልፅ ባለዳረገበትም፤ እሱን ኮንትሮል የሚያደርግ መልስ የማይሰጥ ተሳታፊ የሚኖርበት መድረክ ላለመፍጠር ነው፡፡

ምን ማለትዎ ነው አቶ ዘሪሁን? ግልጽ ያድርጉልን። ሰዎች ነጻ ሆነው አየር ላይ እንዲናገሩ ትክክለኛጊዜው አሁን አይደለም፤ የጠራ ነገር የለም ነው የሚሉት?

አላልኩም! አላልኩም፤ ሰዎች በግልጽ መናገር ይችላሉ። ሰዎች በግልጽ ተናገሩ ማለት ግን የሚናገሩትን በሙሉ ያውቃሉ ማለት አይደለም። አንድ ሚዲያ ላይ የሚተላለፍ ነገር በእንዲህ ዓይነት ወደ ግራ ይሂድ ወደ ቀኝ፣ ወደፊት ይሂድ ወደ ኋላ በማይታወቅ ሁኔታ ላይቭ ከፍተህ እሱን የምታስተናግድና አንጻራዊ በሆነ ደረጃ አቅሙ አላት የምትላት ሆስት በሌለችበት ከፍቶ መልቀቅ አንድም ማምታታት ነው። ሁለተም ማዘባረቅ ነው። ሦስትም መደበላለቅ ነው። ስለሆነም…

ይቅርታ ግን፤ ይህን ፕሮግራም መምራት የሚችሉት ወይዘሮ ሚሚ ብቻ ናቸው እንዴ?

ናቸው። ቆይታ ከሚሚ ስብሀቱ ጋ ነው የሚለው። ከእሷ በፊት የነበረችው የምትችል መስታወት ነበረች። መስታወት ደግሞ ለቃለች። ከዚያ ውጭ ያሉት አዳዲስ ናቸው። መቼም አንተ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ነህ። ስቲቨን ሳከርን የምትተካው ዘይናብ በዳዊ ናት። ሌላ ማንም አይተካም።

ስለዚህ ባለቤትዎ ወይዘሮ ሚሚ እስኪመለሱ ድረስ ያ ቦታ ክፍት ነው የሚሆነው?

በተቻለ መጠን እኮ ተሞክሯል። ሌላ የምትጠይቀኝ ጥያቄ ካለ ጠይቀኝ። አዎ ሚሚ ትመለሳለች፤ አንድ። ፕሮግራሙ ይጀምራል፤ ሁለት። ጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ ይጀምራል? አዎ ይጀምራል። መቼ? የሚቀጥለው 15 ቀን። ከዚያ በኋላ ሚሚ ትመጣለች? አዎ ትመጣለች፡፡ ዛሚ ይዘጋል ወይ? አይዘጋም። በፋይናንስ እጥረት? አይዘጋም።

ፋይናንስ ችግር ግን የገጠማችሁ ይመስላል፤ እንዴት ነው የምትወጡት?

ቢበዛ የምናደርገው ስታፍ እንቀንሳለን። ካልቻልን።

ጋዜጠኞቻችሁ ቁጥራቸው ስንት ነው? ተመናምነዋል እየተባለ ነው

አሁን ላይ? በግምት ወደ 6 አለን።

በቅርቡ ሠራተኛቀንሳችኋል?

እኛ ቀንሰን ሳይሆን ራሳቸውም የሄዱ ልጆች አሉ። በነገራችን ላይ ዛሚ ላይ የነበሩ ጋዜጠኞች ሁሉም ጣቢያ ላይ አሉ። አሀዱ ብትሄድ የእኛ ልጆች አሉ። የጋዜጠኝነት ብኩርናቸውን ከእኛ ጋር የቀደሱ። ሸገር ብትሄድ አሉ። ፋና ብትሄድ አሉ…

ከሰሞኑ ችግር ጋር በተያያዘ የቀነሳችሁት ሠራተኛ ግን የለም?አንድ ነገር ልንገርህ። ዛሚ ዛሚን መዝጋት ካለበት በሶሻል ሚዲያ ስለተወራ አይዘጋም። ዛሚ ዛሚን አይዘጋም። በሦስትም ሰው በአራትም ሰው ከዚያ ውጭ ያለውን በአጋር መሙላት ይቻላል። ስለዚህ የፕሮግራም ትኩረታችን አስተካክለን አንድ ነገር ማድረግ እንችላለን። አማራጩ ክፍት ነው ማለቴ ነው። ዛሬ ላይ ካንተ ጋር እየተነጋገርኩ ዛሚ እራሱን ለመዝጋት እቅድ የለውም። እራሱን አይዘጋም። ሊዘጉት የሚሞክሩ ካሉ አትችሉም ይላቸዋል። ከቻሉ ደግሞ ያኔ እናያለን።

ችግር ላይ ያላችሁ ይመስላል። ጫና እየደረሰባችሁ ይሆን እንዴ? ከመንግሥት አካባቢ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ?

እስካሁን ድረስ ከአዲሱ መንግሥት ጋር በጫናም በፍቅርም የተገናኘነው ነገር የለንም። ከድሮውም ጋር ብዙ የለንም። ጫና የነበረብን ባለፈው ጊዜ ነው ከብሮድካስት ባለሥልጣን፤ እሱ ደግሞ የሚታወቅ ነው።

ስለዚህ ምነም ጫና አልደረሰባችሁም?

መንግሥትነት ግን በሚገርምህ ደረጃ እኮ ቢሮ የያዘ ብቻ አይደለም። ቢሮ የያዘውንም እኔ ነኝ ባለቤቱ የሚልም ሊመጣ ይችላል። ምናልባት ሶሻል ሚዲያ ላይ [ዛሚ ሊዘጋ ነው] ያ መረጃ አለን የሚሉ ሰዎች ከዚያ አካባቢ የመጡ ከሆነ አንተ አጣራቸው።

አሁን ባለው የለውጥ ሁኔታ ይሄ ጣቢያ ምቾት የማይሰጣቸው ሰዎች ጫና ያደርሱብናል ብላችሁ ትሰጋላችሁ?

ለምን እንሰጋለን? ትናንትም የማይወዱን ሰዎች ነበሩ። ዛሬም የማይወዱን ሊኖሩ ይችላሉ። ትናንትም የሚወዱንም ነበሩ፤ ዛሬም የሚወዱን አሉ። በተደራጀ መልኩ መንግሥት ሆነው ይሄንን የሚሞክሩ እስካሁን ድረስ በፊት ለፊት ያገኘናቸው የሉም። ከመጡ ደግሞ እንደ አመጣጣቸው ስማቸውን ጠርተን እንናገራለን።

ሜቴክ ዋንኛ ደጋፊያችሁ ነበር ልበል?

እንኳን ይሄንን ነገር ጠየቅከኝ። በደንብ ስማ። የሚገርም ብዥታ አለ። እስከዛሬ ተናግሬው አላውቅም ይሄንን ነገር። አንደኛ! እኛ ከሜቴክ ጋር ግንኙነት ነበረን? አዎ። ሁለት፤ ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረን? ሜቴክ ለዛሚ ሬዲዮ ጣቢያ በብር የሚቆጠር አንድ ብር፣ አ…ንድ ብ…ር ሰጥቶ አያውቅም። ትሰማኛለህ? አ…ንድ ብር!እኛ መልዕክት የሚያስተላልፍ ጣቢያ ነበረን፤ ስለሆነም ከሜቴክ ጋር የነበረን የዓይነት ልውውጥ ነው። የዓይነት ልውውጥ ምንድነው በለኝ፤ ሜቴክ ጄኔሬተር ሰጠን። ምክንያቱም ፉሪ ላይ ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ ችግረ ነበረብን። ገዝተን የነበረን አቅሙ አነስተኛ የሆነ ጄኔሬተር ተቃጠለ። በ2007 ዓ.ም ማለት ነው።

ስለሆነም እኛ የሜቴክን ማስታወቂያዎች እናስተላልፍ፤ እናንተ ጄኔሬተር ስጡን፤ በሰዓት ማስታወቂያ የምናስተላልፍበት ዋጋ ይኸውና፤ ይሄ ጄኔሬተር በዚህ ወቅት የሚያወጣው ዋጋ ይኸውና፤ ስለሆነም በአገልግሎት ልውውጥ እናጣጣው ተባባልን። አ…ንድ ጄኔሬተር ነው ሜቴክ የሰጠን። ከዚያ ውጭ አስክሜቴክ፤ አስክ ማንንም ሰው ለዛሚ ፐብሊክ ኮኔክሽን ሜቴክ ይሄንን ሺህ ከፈለ የሚል ካገኘህ ይዘህ ና።

ለአንድ ጄኔሬተር ስንት የአየር ሰዓት አገኙ?

162 ሰዓት! ኢንፋክት አሳልፈን ሰጥተናቸዋል። ሌላ ጥያቄ ካለህ ጠይቀኝ

ከቀድሞው የደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራችሁም?

ሊዘጋ ነው ከሚል ጀምረህ ነው አሁን ይህን የምትጠይቀኝ፣ አይደል? ቢኖረን ኖሮ እስካሁን ሳይወጣ የሚቆይ ይመስልኻል? አንተው መልሰው፤ ቢኖረን ኖሮ እስካሁን ዝም የሚባል ይመስልኻል? የለንም። አልነበረንም። እንደ ማንኛውም አንተ ዛሬ ከማንም መረጃ እንደምትሰብስበው እኛም በጊዜው ከማንም መረጃ እንሰበስባለን፤ ከማንኛውም መረጃን እንቀበላለን፤ እሱም የኢትዮጵያ ደኅንነት መሥሪያ ቤትን ይጨምራል፡፡ ዕድሉ ካለን ነገም እንወስዳለን።

ዛሚ ከዐብይ በፊት ከነበረው አመራር ጋር በቅርብ የሚሞዳሞድ ጣቢያ እንደሆነ ነው የሚነገረው፤ አሁን ደግሞ ሥልጣን ላይ ያሉት ዛሚ በብዛት ሲተቻቸው የነበሩ ናቸው፤ እነሱን እየተቻችሁ ትቀጥላላችሁ?

ምንድነው የደገፍነው ቆይ እኛ…? ዛሬ ላይ በሥልጣን ላይ ያሉ ባለሥልጣኖቻችንን እነሱንም የሚደግፉ፣ በጥቅምም በሌላ መልኩም የሚደግፉ ሰዎች ካሉት ውጭ ምን አልን? ማለቴ ሕገ መንግሥት አለ በዚች አገር፤ ሕገ መንግሥት ይከበር፣ የሕግ የበላይነት ይከበር፣ ብጥበጣ አይበጀንም፣ ሰዎች አይገዳደሉ ነው ያልነው፤ አይደለም እንዴ? ዛሬም እሱ ነው እኮ ጩኸቱ…። አዎ ይሄ ከሆነ መለኪያው እንደ ሁሉም ሰው ደጋፊ ነን ማለት ነው። ከዚያ ውጭ ግን አገሌ ከፍሎን አገሌ ሰጥቶን… ማለቴ እኛ እቃ አይደለንም እኮ።

ስለዚህ ስናጠቃልለውአቶ ዘሪሁን፤ የፋይናንስ ችግሮች የሉባችሁም፤ ቢኖሩም አዲስ ነገር አይደለም።ስፖንሰር ክፍያ መዘግየት ካልሆነ

ስፖንሰር መዘግየት፣ ስፖንሰር መቀነስ፣ የፋይናንስ ችግር አዎ አሉብን። አጋጥመውናል። አጋጥመውንም ያውቃሉ። ዛሬ ብቻ አይደለም።

አቶ ዘሪሁን ይህ ክስተት ለውጡን ተከትሎ የመጣም አይደለም ነው የሚሉኝ አይደለም? የስፖንሰሮቹ መሸሽ ለውጡን ተከትሎ የመጣ እንዳይሆን?

ድሮም እኮ ያንን ያህል የቀረቡ የሉም፤ ዘንድሮም ያንን ያህል የሸሹ የሉም። ለምን እንደሚቀርቡ፣ ለምን እንደሚሸሹ አናውቀውም።

በመንግሥት ነው ስላልከው፣ ነገርኩህ እኮ! ገንዘብ የምታገኙት ከደኅንነት ነበር ላልከው ከደኅንነት ያገኘነው አምስት ሳንቲም የለም፤ መረጃ ካላችሁ አውጡት፤ ሜቴክ ጋር በተመለከተ አምስት ሳንቲም የገንዘብ ክፍያ የለንም። የወሰድነው ጄኔሬተር ነው፤ ይህንን ሜቴክ ያውቃል። አገልግሎት ሰጠነው፣ በሚመጥነው ዋጋ፤ አበቃ!

አሁን ዛሚ እንደማይዘጋ ማረጋገጫ ይሰጡኛል?

ቆይ በግልጽ ላስቀምጥልህ! እንዴ ዛሚ ሊዘጋ ይችላል እኮ! ወይ እኔ ልሞት እችላለሁ? ወይ አንዱ ተነስቶ ዝጋው ሊለን ይችላል ወይ… ነገርኩህ የሁለት ቀን የደመወዝ መዘግየት አጋጠመ፤ ከዚያ ውጭ እንግዲህ ለመዝጋት ያሰቡ ካሉ እናያለን።ትናንትም በማስጠንቀቂያ ተሞክሮ አልተዘጋም፤ ነገም በማስጠንቀቂያ ተሞክሮም ወይም ተገፍቶም እንዝጋቸው እስካላሉን አንዘጋም።

ወይዘሮ ሚሚ ስብሐቱ የት ናቸው በትክክል? ወደ ጣቢያውስ ይመለሳሉ ወይ?

እንዲያውም ልንገርህ፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የ”ጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ” እንደሚጀምር እናስታውቃለን፤ የሚቀጥለው እሑድ እንዲያውም የመጀመርያ እንግዳችንን ከቢቢሲ እና ከሌሎችም ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ሚዲያ ውስጥ የመሥራትን ጥቅምና ጉዳት እንዲያወሩን እንጋብዛለን። ምናልባት አንተ ወይም አለቃህ እንግዳችን ይሆናሉ፤ ኦኤምኤንን ጨምሮ…

ወይዘሮ ሚሚ ይመሩታል?

የአሁኑ ሳምንት [ሆስት የማደርገው] የማስተናብረው እኔ ዘሪሁን ተሾመ ነኝ፤ ከጥቅምት [ኦክቶበር] መጨረሻ በኋላ ወይዘሮ ሚሚ ይሆናሉ።

ወይዘሮ ሚሚ ላለፉት ጊዜያት ያልነበሩበት ምክንያት ግን አልነገሩኝም?

የግል ጉዳይ ነው፤ የጤንነት ጉዳይ ነው፤ ዋናው ደግሞ የዓይን ጉዳይ ነው፤ ስለዚህ ዓይኗን መታከም ነበረባት፤ ዓይኗን ታክማ ተደጋጋሚ ነገር መደረግ ነበረበት፤ በእሱ ሁኔታ መብረር አይፈቅድም ከዚያ ደግሞ አቧራው ትንሽ የቀነሰ ቦታ መቆየት ነበረባት፤ እናም አሜሪካ ነው የቆየችው።

ላለፉት ስድስት ወራት?

ስድስት ወር አይሆንም አምስት ወራት ቢሆን ነው፤ ግንቦት መጨረሻ ነው የሄደችው። ሕይወትን የሚያህል ነገር በተለይ ዓይን ከዚያ በላይ ቢወስድም የሚገርም ነገር የለውም፤ እንዳልኩህ ነው ተደጋጋሚ ሰርጄሪ ያስፈልግ ነበር፤ ሁለተኛው [ህመሟ] አቧራ አይፈልግም፤ በዚህም ምክንያት እዚያ መቆየት ነበረባት፤ ይሄን አቧራ የፖለቲካ አቧራ ብላችሁ ከተረጎማችሁትም እኔ የለሁበትም፡፡ (ሳቅ)

ስለጊዜዎ እናመሰግናለን አቶ ዘሪሁን

ምንም አይደል፡፡

ምንጭ: ቢቢሲ የአማርኛው ዜና አገልግሎት

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.