Monday, March 30, 2020
Home > ዜና > ሁሉም ይስማ፤ በአገራችን ቀልድ የለም! – ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ

ሁሉም ይስማ፤ በአገራችን ቀልድ የለም! – ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ

ውድ ወዳጆቼ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን! እስኪ ለአገራችን ይበጃሉ በምንላቸው ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ እንጋራ። ዕድሜውን አድሎን በዚያኛው ዘመን የነበርን ሰዎች ‘ትግሉ ረዥምና መራራ ነው’ የምትለውን አባባል እናስታውሳታለን።

ማስተዋል ለፈለገ ታዲያ ዛሬም ረዥምና መራር ትግል ከፊታችን የጋረጠ በእናት ኢትዮጵያ ልጆች ህይወትና የነገ ዕጣ ፈንታ ላይ እየተወራረደ ያለ ሰው ሠራሽ አደጋ መኖሩ አይጠፋውም። ባለቤቶቹ እነማን ናቸው ነው ጥያቄው። አክራሪው በዝቶ አግራሪው ለምን አነሰ? ደግሞስ ለምን አልደመጥ አለ?

እያየን እንዳለነው ዋና መዲናችንን ጨምሮ በአገራችን በርካታ ቦታዎች ከማሕበራዊ ሰላም እስከ በሕይወት የመኖር ዋስትና ለምን በቋፍ ላይ ሆነ? ለምን በአንጻራዊ የዴሞክራሲ እና ማሕበራዊ ፍትሕ መባቻ ላይ ነን ብለን ባሰብንበት ወቅት ነገሮች የተካረረ ጽንፍ ያዙ? ለምንስ ድንጋይ አቀባይ ‘የእብድ ገላጋይ’ በዛ? ይህ ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ የፖለቲካ ሸፍጥና ንግድ እንዴት እንዲህ በማናለብኝነት ተደላደለ? ወዘተ…

እነዚህና መሰል ጥያቄዎች ሲያብሰለስሉኝ ከወዳጆቼ ጋር ለማውጋት እሞክራለሁ፤ አዳምጣለሁ። በዚህ ዕሳቤ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ከሆኑት ፕ/ር መረራ ጉዲና ጋር የዛሬውን የምሳ ሰዓቴን አብሬያቸው በመሆን (የምሳው ከፋይ እሳቸው…) ለማሳለፍ ሞክሬያለሁ።

በእንደዚህ ዓይነት መደበኛ ያልሆኑ ቆይታዎች እዚህም እዚያም የሚረግጡ ሃሳቦች መነሳታቸው ስለማይቀር ስለቆይታችን በሙሉ ለመዘከር አልችልም። ሆኖም ከሰውየው የፖለቲካ ዕውቀት፣ ልምድና በሕዝብ ውስጥ ካላቸው የማንነት ካፒታል አንፃር ያጋሩኝን ጥቅል አስተያየት ለfb. ወዳጆቼ በሚጠቅም መልኩ ብሰነዝር ደስ ይለኛል። እና ሃሳብ እናንሸራሽርበት ለማለት ጭምር ነው።

አሁን እየሆነ ያለውን አገር የሚያጠፋ የነገር ተዋናዮች ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። መንግስትም ጠንቅቆ ያውቃቸዋል። አሠራራቸው ምንም ሰምና ወርቅ የሌለው፣ በጠራራ ፀሐይ የሚከናወንና በፖለቲካ ስሌት ‘ቆይ እስኪ’ እየተባሉ ያበጡ ናቸው። ሶስት ነገሮችም አመቺ ሆነውላቸዋል።

አንደኛው የሕዝቡ በመሰል ሁነቶች ላይ ‘እምቢኝ’ ብሎ ከመነሳቱ በፊት ‘ባለጌም ቢሆን የእኛው ባለጌ ነው’ ዓይነት ጊዜ ሰጥቶ ነገሮች ይስተካከሉ ይሆናል በሚል የሚያሳየው ወላጃዊ ሆደ ሰፊነትና ተስፋ ነው።

ሁለተኛው ‘የዘገየ ፍርድ እንደተከለከለ ይቆጠራል’ የሚለውን የሕግ መርሕ በፖለቲካ ስሌት ወደጎን አድርጎ ፖለቲካዊ መፍትሔዎች ላይ እያተኮረ ያለው የመንግስት አሠራር የፈጠረው ፋታ ሕዝቡን በመከራ ማጥ ውስጥ ለ27 ዓመታት ዘፍቀውት ለኖሩት ‘የቀን ጅቦች’ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርቆ ከቀበራቸው መቃብር፤ በማተረማመስ ግርግር ቀቢፃዊ ተስፋ አፈራቸውን አራግፈው፤ ቢቻል ወደነበሩበት ማማ፤ ባይቻል ከነህልቆ መሳፍርት ወንጀላቸው ሳይነኩ ርቀታቸውን ጠብቀው መኖር ነው።

ሶስተኛው የሕዝብ አይንና ጆሮ የሆኑ ሚዲያዎችና ባለሙያዎች ፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ፣ ምሁራንና ሌሎችም በተለያዩ ምክንያቶች አርምሞ ላይ መሆናቸው ነው።

እነዚህ ሶስቱ፤ ቶሎ እና የሚገባውን ያህል ተቀናጅተው መሥራት የጀመሩ ቀን የተጋረደብን ጭጋግ ገለል ማለቱ የግድ ነው! እና ዜግነታዊ ሃላፊነትን የመወጣት የውዴታ ግዴታ ጥሪ ጭምር ነው ማለት ነው። ማድረግ የምንችለው፤ ደግሞም የሚገባን ትልቅ ወቅታዊ ተግባር ነው።

ይህንን እያልንና እያደረግንም የእኩይ ድርጊት ልሂቃኑን ልቦና እንዲሰጣቸው እንጸልያለን። በአገራችን ግን ቀልድ የለም! ለትንሳኤዋ፣ ለክብሯና ለልዕልናዋ እንደማናንቀላፋ ሁሉም ይስማ!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!

በውብሸት ታዬ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.