Sunday, April 5, 2020
Home > ዜና > አዲሷ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማን ናቸው? – BBC News

አዲሷ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ማን ናቸው? – BBC News

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎች ላይ ሴቶች የተሾሙ ሲሆን ከሃያዎቹ ሚኒስትሮች አስሩ ሴቶች ሆነዋል። ይህ ሁኔታ በማህበረሰቡ ዘንድ የተደበላለቀ ሃሳብን ቀስቅሷል።

ሹመቱን በአዎንታ የመታየቱን ያህል፣ ከዚህ በፊት ወንዶች ሚኒስትሮች ላይ ተነስተው የማያውቁ የብቃት ጥያቄዎችና ሹመቱ ከውክልና ያለፈ ምንም አይነት ፋይዳ የለውም የሚሉ ሃሳቦችም እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ።

በተለይም “ሴት ስለሆኑ ብቻ የብቃት ጥያቄዎችን የሚያነሱትን” አስመልክቶ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋየ የማህበረሰቡ ስር የሰደደ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማየት ባህልና አመለካከት ጋር በማያያዝም ቀስ በቀስ እንደሚቀረፍ ይናገራሉ።

“ከምሳሌዎቻችን ብንጀምር ሴት ምን ብታቅ በወንድ ያልቅ እያልን እየተናገርን ስላደግን በሙያም ላይ ሴቶችን አሳንሶ የሚያይ የማህበረሰብ ክፍል ይኖራል፣ መሪነት ላይ ሲመጡ ሊሰናከሉ ይችላሉ የሚል አስተሳሰብም አለ።” ሆኖም ግን ይላሉ ሚኒስትሯ “ግን ኃላፊነት ላይ የመጣንና እድሉን ያገኘን ሴቶች በብቃት ስንወጣ ደግሞ ያንን አስተሳሰብ እየሰበርን እንሔዳለን” ይላሉ

ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ የማህበረሰቡ አስተሳሰቦች በዓመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ ተቀርፈዋል ብለው የሚያምኑት ዶ/ር ኤርጎጌ የአሁኑ ሹመትም አንዱ ማሳያ እንደሆነ ይናገራሉ።

“አሁን በተደረገው ሹመት ሴቶች ከወንዶች እኩል ብቻ ሳይሆን በብቃት የተሻለ መስራት እንደሚችሉ፤ ሴት ወንድ የሚል ነገር ሳይሆን ሰው በርትቶ ከሰራ የተሻለ ብቃት ማሳየት ይቻላል።” ይላሉ

ከራሳቸው ልምድ በመነሳትና እንዲሁም ሌሎች ተሿሚዎችን በማየት “በብዙ ፈተናዎች ያለፍን ነን” የሚሉት ሚኒስትሯ “በተለያዩ አካባቢዎች ስንሰራ አይችሉም ወድቀው ይቀራሉ የሚለውን አስተሳሰብ መቀየር ችለናል” በማለት ይናገራሉ ።

የአሁኑንም ሹመት ታሪካዊና በአገሪቷ ደረጃ ትልቅ እርምጃ ከመሆኑ አንፃር የማህበረሰቡን አስተሳሰብ ለመቀየርም የሚያስችል እንደሆነ ያምናሉ።

ባለትዳርና የአንዲት ሴት ልጅ እናት የሆኑት ዶ/ር ኤርጎጌ ተወልደው ያደጉት ሆሳዕና ከተማ ሲሆን፤ አንደኛና ሁለተኛ ክፍልን በሆሳዕና ተምረው ቤተሰቦቻቸው ወደ አዲስ አበባ በስራ በመዛወራቸው ምክንያት ከሶስተኛ እስከ 10ኛ ክፍል አዲስ አበባ ተምረዋል።እንደገና ቤተሰቦቿቸው ወደ ሆሳዕና በመመለሳቸውም ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት ደግሞ ሆሳዕና ዋቸሞ ትምህርት ቤት ነው።

በመቀጠልም ሐዋሳ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በእንግሊዝኛ የቋንቋ ትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ ከተመረቁ በኋላ ጊምቢቹ በሚባል ወረዳ ለሁለት ዓመት ያህል በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት አገልግለዋል።

ለቀጣይ ትምህርትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በውጭ ቋንቋዎች ዘርፍ ዲግሪያቸውን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በስርዓተ- ፆታ፣ እንዲሁም ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በአንትሮፖሎጂ የትምህርት ክፍል የግጭት አፈታት ህንድ በሚገኘው የአንድራ ዩኒቨርስቲ ተምረዋል።

የስራ ህይወታቸውን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማስተማር የጀመሩት ዶ/ር ኤርጎጌ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት የስርዓተ- ፆታና የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክተርነት አገልግለዋል።

በተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ፣ የተለያዩ አገር በቀል ድርጅቶችን በማማከር ስራ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የልጃገረዶች ትምህርት (ገርልስ ኤጁኬሸን አድቫይዘሪ ኮሚቴ )፣ በስርዓተ- ፆታ ፖሊሲ አማካሪነትም ሰርተዋል።

ከዚሀም በተጨማሪ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኤችአይቪ ኤድስ ላይ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ፣ ከኢፌዲሪ የሰላም ማስከበር ተቋም፣ ዩኤንዲፒ፣ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን በግጭት አፈታት ላይ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት፣ ለሁለት ዓመታት ያህልም በሶዶ ዩኒቨርስቲና በተለያዩ የልማት ድርጅት በቦርድ አባልነት ኃላፊነቶች ላይ ነበሩ። በሚኒስትርነት ከመሾማቸው በፊት የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ።

ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ምን አይነት ተግባሮችን ለማከናወን ዕቅድ ይዘዋል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ከተማሩት ትምህርትንና ያገኟቸውን የስራ ልምዶች በማገናኘት ሰፊ ስራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

“የተቋሙ የራሱ ራዕይ አለው ያንን ማሳካት እንዲሁም መዋቅራዊ ለውጦች የሚያስፈልግም ከሆነ በጥናት በተደገፈ መልኩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሻለ አገልግሎት መስጠትና ህዝብን ማገልገል ይቻል ዘንድ የተለያዩ ስራዎችን እሰራለሁ ብየ አስባለሁ” ብለዋል።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.