Sunday, April 5, 2020
Home > ዜና > የራያ ተወላጆች በአላማጣና ቆቦ መንገዶችን ዘጉ! – ESAT

የራያ ተወላጆች በአላማጣና ቆቦ መንገዶችን ዘጉ! – ESAT

የራያ እናቶች ታፍሰው የተወሰዱ ልጆቻቸው እንዲፈቱ በመጠየቅ ላይ ናቸው።

የትግራይ ክልል መስተዳድር በራያ ላይ እየወሰደ ያለውን ርምጃ በመቃወም ለፊታችን እሁድ በጎንደር ሰልፍ ተጠርቷል።

በሌላ በኩል የማንነት ጥያቄዎች እየቀረቡ ያሉት ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ በመሆኑ መልስ ለመስጠት አልተቻለም ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ገለጹ።

አፈ ጉባዔዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የወልቃይትም ሆነ የራያ የማንነት ጥያቄ ካለ በቅድሚያ መቅረብ ያለበት ለትግራይ ክልል መሆኑንም ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅሰዋል።

የራያው ተቃውሞ ለአምስተኛ ቀን ቀጥሏል። በትግራይ ልዩ ሃይል ተጠናክሮ በመካሄድ ላይ ያለው አፈሳ መቀጠሉን በመቃወም በተለያዩ አካባቢዎች መንገዶች እየተዘጉ መሆናቸውን ነው የደረሰን መረጃ ያመለከተው።

በአላማጣ፣ ቆቦና መሆኒ የተሽከርካሪ መተላለፊያ የሆኑ መንገዶች በተለያዩ የድንጋይና የዛፍ ክምሮች መዘጋታቸው ታውቋል።

በተለይም ወደ መቀሌ የሚወስዱ መንገዶች ዒላማ እንደተደረገባቸው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

መንገድ መዝጋቱ ሁለት ዕላማዎች እንዳሉት የገለጹት ነዋሪዎች በዋናነት የራያ ተወላጆች ታፍሰው ወደ ተለያዩ የትግራይ እስር ቤት የሚወሰዱ ተሽከርካሪዎችን መግታት እንደሆነ ታውቋል።

በተጨማሪም በጅምላ ታፍሰው በየእስር ቤቱ የታጎሩ የራያ ተወላጆች እስኪፈቱ መንገድ መዝጋቱ የተቃውሞ መግለጫ እንዲሆን ታቅዶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ነው ለኢሳት ከደረሰው መረጃ ለማወቅ የተቻለው።

መንገዶችን ለማስከፈት በተደረገ የሃይል ርምጃ በትግራይ ልዩ ሃይልና በራያ ወጣቶች መካከል ግጭት መፈጠሩም ተገልጿል።

በአምስት ቀናቱ የትግራይ ልዩ ሃይል ርምጃ የታሰሩትን የራያ ተወላጆች ቁጥር በትክክል ለማወቅ እንዳልተቻለ የራያን ጉዳይ የሚከታተለው ኮሚቴ ገልጿል።

በትንሹ 500 የሚሆኑ የራያ ተወላጆች ማይጨውን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ እስር ቤቶች እንደታሰሩ ከኮሚቴው አካባቢ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የራያ እናቶች የልጆቻቸው ሁኔታ ስጋት ውስጥ የከተታቸው መሆኑን በመጠቀስ የፌደራል መንግስት ምላሽ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።

በሰሞኑ አፈሳ የራያ ባለሃብቶችንና ታዋቂ የሀገር ሽማግሌዎችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የራያ ተወላጆች መታሰራቸው ይታወቃል። 5 ሰዎችም በትግራይ ልዩ ሃይል በተተኮሰ ጥይት መገደላቸው የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል በራያ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በመቃወም በጎንደርና በወልድያ ሰልፍ ተጠርቷል።

በራያ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ይህን ግፍ በመቃወም በመላው አማራ ሰልፍ ሊካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑም ተሰምቷል።

የፊታችን እሁድ ጥቅምት 18/2011 ዓምተምህረት የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ፡ የራያን የማንነት ጥያቄ በሃይል ለመፍታት የትግራይ ክልል መንግስት የሚወስደውን የጭካኔ ርምጃ እንዲያቆም ለመጠየቅ መሆኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ በደሴ የተቃውሞ ሰልፍ መጠራቱ እየተነገረ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ስለራያ ማንነትን የተመለከተ ጥያቄ አልቀረበልንም ሲሉ ገለጹጸዋል።

አፈጉባዔዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ራያንም ሆነ ወልቃይትን በተመለከተ የማንነት ጥያቄ መቅረብ ያለበት በቅድሚያ ለትግራይ ክልል መንግስት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የማንነት ጥያቄዎች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መቅረብ ያለባቸው ጥያቄውን የሚያነሱ ዜጎች በሚኖሩበት ክልል ከታየ በኋላ ነው ብለዋል አፈ ጉባዔዋ።

የወልቃይት ማንነትን በተመለከተ ለትግራይ ክልል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም በምላሹ የአፈና ርምጃ መወሰዱን የሚገልጹት አንድ የወልቃይት ማንነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ህወሃት የወልቃይትንም ሆነ የራያን የምንነት ጥያቄዎች ለመመለስ የሚችል አይደለም ይላሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ የህወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል መሆናቸው ይታወቃል።

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.