Wednesday, January 22, 2020
Home > ዜና > ‹ከእልህ አስጨራሽ የእርስ በርስ ጦርነት እና ከአስከፊ ድርቅና ርሃብ ወጥታ የዓለምን ቀልብ የሳበች ምስራቅ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ››

‹ከእልህ አስጨራሽ የእርስ በርስ ጦርነት እና ከአስከፊ ድርቅና ርሃብ ወጥታ የዓለምን ቀልብ የሳበች ምስራቅ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ››

ዴቪድ ሞኒያ የተባሉ የጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ያቀረቡት አተያይ በጨረፍታ ሲዳሰስ፡፡ዴቪድ ሞኒያ በጀሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኝ እና መምህር ናቸው፡፡ በልጅነት ዘመናቸው የነበራቸውን የአፍሪካ ሀገራት ትውስታ እንዲህ ይገልፁታል፡፡ በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት የ10 ዓመት ገደማ ልጅ ነበርኩ፡፡ አስታውሳለሁ ኢትዮጵያ በአፍሪካ መጥፎ የተባለለትን የድርቅ፣ ርሃብ፣ ጦርነት፣ ቸነፈር እና በሽታን ታስተናግድ ነበር፡፡

ይህ ወቅት አሜሪካዊያን የቀዝቃዛውን ጦርነት በበላይነት መቋጨታቸውን ተከትሎ ‹ወርቃማ ዘመን› ብለው የሚያከብሩበት ጊዜ ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካም ምንም እንኳን የአውሮፓዊያን ፊልምና ሙዚቃ መዝናኛችን እንደሆነ ቢቀጥልም የነፃነት እንቅስቃሴው ከቀድሞ ጨቋኝ አገዛዝ እራሱን ነፃ አድርጎ የተንቀሳቀሰበት እና ለውጥ የሚፈልግበት ወቅት ነበር፡፡

አስታውሳለሁ አሉ ሞኒያ ‹‹በዚህ ወቅት ነበር በኢትዮጵያ ስለተከሰተው አስከፊ ርሃብ እና ድርቅ የሰማሁት፡፡›› በፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለ ማሪያም አገዛዝ ስር የነበረችው አፍሪካዊት የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ኢትዮጵያ በሶማሊያው አቻቸው ፕሬዝዳንት ሲያድ ባሬ ከሚመራው ጦር ጋር ከፍተኛ የሆነ የሞት ሽረት ጦርነት ያደረገችው፡፡

ከዚያ በኋላ ሶማሌ እና ኢትዮጵያ በተለያየ ሀገራዊ ገፅታዎች ላይ ናቸው፡፡ ሶማሌ በፕሬዝዳንቷ ሲያድ ባሬ መሪነት የጀመረችውን ጦርነት በሽንፈት ካደማደመች በኋላ ለወሬ ነጋሪ ጥሪት ያልተረፋት እና የተበታተነች ሀገር ሆናለች፡፡ ኢትዮጵያ በአንፃሩ የደርግን ስርዓት አስወግዶ መንበሩን የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) እንደገና አዋቅሮ ሀገሪቱን የማስቀጠል ስልጣን ተረክቦ ይመራታል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ከቀድሞ መታወቂያዋ ጦርነት፣ ቸነፈር እና እርዛት ወጥታ ወደሌላ የአፍሪካ አህጉር ተምሳሌትነት ተሸጋግራለች የሚሉት ሞኒያ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በተለያዩ እጅግ አንፀራቂ ተግባራት ዳግም ወደ አፍሪካ መሪነቷ ለመመለስ ትክክለኛው መንገድ ላይ ያለች ሀገር ትመስላለች ይላሉ፡፡ በመልካ ምድራዊ አቀማመጧ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው ቀዳሚዎቹ ሀገራት መካከል ትመደባለች፡፡ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2016 በነበረው የህዝብ ቁጥር መረጃ መሰረት 102 ሚሊየን ህዝብ በመያዝ ከናይጀሪያ ቀጥላ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት፡፡

መልካምድራዊ አቀማመጧ ለመካከለኛው ምስራቅ ቅርብ በመሆኗ የዓለምን ማጣኔ ሃብት በሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ለሚመሩት ቻይና እና ጃፓን መልካም መደረሻ ናት ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ግስጋሴዋ ከቀጠለች በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ለመድረስ ያላትን ህልም እውን ለማድረግ የሚያግዳት ነገር አይኖርም ይላሉ የፓለቲካ ተንታኙ ሞኒያ፡፡

ከ2005 ጀምሮ አማካይ 10.3 በመቶ ሀገራዊ እድገት አላት የሚሉት ተንታኙ ይህም ዕቅዷን በተሳካ ሁኔታ እንደምታሳካ ማረጋገጫ ነው ባይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ አትራፊ የአየር መንገዶች ውስጥ አንዱና ቀዳሚው ነው፡፡ አፍሪካ አሉኝ ከምትላቸው አየር ምንገዶች ውስጥ የደቡብ አፍሪካ፣ የኬኒያና የኢትዮጵያ አየር መንገዶች ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ የጀመረው እና ከአዲስ አበባ ከተማ በ48 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቢሾፍቱ አካባቢ የሚገነባው የአየር ማረፊያ በየዓመቱ 80 ሚሊየን ተጓዦችን የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡ ይህም ይላሉ ሞኒያ በዘርፉ ኢትዮጵያ አቢዎት ውስጥ መሆኗን ያሳያል በቀጣይም መሪ የሆነ የአየር መንገድ ታሳየናለች ነው ያሉት፡፡

የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር. ዐብይ አህመድ ለተወሰኑ ዓመታት በፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የቆየችውን እና በተወሰኑ ዓመታት የውስጥ ሰላም የራቃትን ሀገር ሊያረጋጉ የመጡ መሪ ይመስላሉ፡፡

የሰላም ጉዟቸው ፀበል ለህዝባቸው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያንም እያደረሰ ነው የሚሉት ተንታኙ ማስረጃ ከሚሏቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱ ደግሞ ለሁለት ዓስርት ዓመታት በጦርነት እና በጥላቻ የዘለቁትን የኤርትራን እና የኢትዮጵያን ቁርሾ መፍታት ችለዋል ይላሉ፡፡

ወደ ስልጣን እንደወጡ ለእንደራሴዎቻቸው በገቡት ቃል መሰረት ወደ እርቅ ለማምራት ጊዜ አልወሰደባቸውም የሚሉት የፓለቲካ ተንታኙ ሞኒያ የቀጣይ ዕቅዳቸው በጦርነት የተጎሳቆለውን የሁለቱን አካባቢ ህዝቦች ወደለየለት የኢንዱስትሪና የንግድ ቀጠና ለማሸጋገር ያቀዱ ይመስላሉ ይላሉ፡፡

በቅርቡ ለሹመት ያቀረቧቸው እንስቶች ቁጥር እና አዲስ ሴት ርዕሰ ብሔር መሾም አሁንም ኢትዮጵያ በአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት የመሪነት ቦታ ላይ ለወንዶች ብቻ የተሰጠውን የርስት አስተሳሰብ መቀየር ችለዋል ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በዚሁ ግስጋሴዋ ከቀጠለች ግንባር ቀደም የቻይና መዳረሻ እንደምትሆን የተነበዩት ሞኒያ የአፍሪካዊያን የአምራቹ ዘርፍ እምብርትም ትሆናለች ብለዋል፡፡ እስካሁን ባለው የንግድ ሚዛን የዓለማችን የንግድ እንቅስቃሴ ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አበረታች እና ታዳጊ ኢኮኖሚን በሚመሩት ደቡብ አፍሪካ እና ናይጄሪያ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ የዓለም የንግዱ ሚዛን ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም ነው ያሉት፡፡

ምንጭ፡- አይ ኦ ኤል

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.