Friday, December 6, 2019
Home > ማህበራዊ > የሚቀጥለው ምርጫ ላይካሄድ ወይም ሊካሄድ ይችላል እየተባለ ነው

የሚቀጥለው ምርጫ ላይካሄድ ወይም ሊካሄድ ይችላል እየተባለ ነው

በሀገራችን ፖለቲካ ትንታኔ አንቱታን ያተረፉ በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን አሁን ሃገራችን ያለችበትን ወቅት “አደገኛ” ሲሉ ይገልፁታል። በበሳል ምልከታቸውና በገለልተኛ ትንታኒያቸው ከባድመ ከንቱ ጦርነት ዋዜማ ጀምሮ የማውቃቸው ፕ/ር መድህኔ ታደሰም ከጥቂት ወራት በፊት ከአንድ ሀገር በቀል የቴሌቩዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ላይ ይሄንኑ ስጋት አመላክተዋል።

“ብሄራዊ መግባባት የለንም ላንዳንዶች ጀግና የሆነው ለሌላው አካል አሽባሪ ነው፣ሁላችንም ብሄራዊ ጀግና አርገን በጋራ ‘አንቱ’የምንለው ሰው የለንም ፣ በሰንደቃላማ ላይ ልዩነት አለን፤ ሁላችንን ለያሰባስብና ሊያግባባ ወደሚችል ደልዳላ ሜዳ ላይ ለመገኘት ብዙ መስራት ያስፈልጋል። ይህ ሳይፈጠር የሚደረግ ምርጫ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል” ቃል በቃልም ባይሆን በደምሳሳው የቃላመጠይቃቸው ጭብጥ እንዲህ የሚል ነበር።

የግንቦት ሰባቱ ሊቀመንበርና ቱባ ፖለቲከኛ ዶር ብርሃኑ፡ነጋም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ብርቱ ወግ”በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ቀርበው “ሲዖልና ገነት ከደጃችን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ምርጫ ማድረግ ብቻ ወዳሰብነው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊያሸጋግረን እንደማይችል ይልቅስ ምርጫው የሚደረግበት መንገድ፣….ከምርጫው በኋላ የምርጫውን ውጤት በፀጋ የመቀበል ከልብ የመነጨ ስምምነት ላይ አስቀድመን ካልደረስን የምርጫው ማግስት ፍፁም ወደለየለት የሲዖል ጥልቅ መንገድ ይዞን እንዳይወርድ ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል። የምርጫው ወቅት እንዲራዘም እንደሚፈልጉና ለዛም የበኩላቸውን እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

የለውጡ ሞተርና መሃንዲስ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ክቡር አቶ ለማ መገርሳም የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማትን በተቀበሉበት ዕለት “አሁንም ሃገራችን መንታ መንገድ ላይ ነች” ሲሉ ተስፋና ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ይህ ስጋት ያለምክንያት የመጣ #ሟርተኝነት አይመስለኝም።
ህወሀት የክልሉን ህዝብ አግቶ ከመገንጠል ባላነሰ ሁኔታ ለማዕከላዊው መንግስት በያዝ ለቀቅ አልታዘዝ ማለት ከጀመረ ሰነበተ። ከአማራው ክልል ጋርም በቃላት ጦርነት መጠዛጠዝ ከጀመረ ቆየ።በሁለቱ ክልልሎች ያለው ውጥረትና የቃላት ውርወራው ወደ ለየለት ግጭት ሊያመራ በቋፍ ያለ ነው የሚመስለው።

“ጠላት ከሩቅ አይመጣም”እንዲሉ የኦሮሞ ፅንፈኛ፡ብሄርተኞች በዶር አብይ መንግስት ላይ ግልፅ ተቃውሞና ተገዳዳሪነትን ማሳየት ከጀመሩ ወራቶች ተቆጥረዋል። ይህን ልብ ያሉት ዶር አብይም በፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ “ከጠላቶቻችን ጋር በስውር፡እያበራችሁ ያላችሁ…” ብለው ማስጠንቀቂያ አዘል ውረፋ እስኪሰነዝሩ ድረስ ህመሙ ዘልቋቸው ገብቶ ነበር። አሁንም ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል።

ይህ ባለበት ሁኔታ ታዲያ ዶር አብይ ምርጫው በታቀደለት የግዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ አጥብቀው የፈላጉበት ምክንያት ምንድነው?…..ምርጫው ካስፈለገ ለአመት ወይም ከዚያ በላይ ቢዘገይስ ምንችግር አለው?…..ድምፃችንን ሰጥተን ባንመርጣቸውም ልባችንን ገብረን “ሺህ አመት ይንገሱ” ስንል ፈቃድ የሰጠናቸው ንጉሳችን ናቸው እኮ እርሳቸው?

የኔን መላምት ከማቅረቤ በፊት ዶር አብይ ምርጫውን አጥብቀው የፈለጉበት ምክንያት የገባው ካለ ቢነግረኝ ደስተኛ ነበርኩ። በኔ ግምት ሰላምን የማይወልድ ፣ ካለንበት ቁልቁል ይዞን ሊወርድ የሚችል አደጋን የፀነሰ ምርጫ ጥንቅር ብሎ ይቅር……። ሰላማዊ ምርጫ ማካሄድ በራሱ ግብ አይደለም። ውጤቱን አሜን ብሎ የሚቀበል መንፈስ በሁሉም ዘንድ ካልሰረፀ።

በመንግስቱ መ ፅዮን

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.