Monday, May 25, 2020
Home > ዜና > አሁን እኛ እስኪ ራሳችንን እንየው መንፈሳዊ ነን ወይስ መንፈሳይ?

አሁን እኛ እስኪ ራሳችንን እንየው መንፈሳዊ ነን ወይስ መንፈሳይ?

መንፈሳዊነት ምንድነው ?
በዲያቆን ዳንኤል ክብረት
=================
ለመሆኑ መንፈሳዊነት ምንድን ነው፡፡ ረዥምቀሚስ መልበስ ነው? ፀጉርን በአሮጌ ሻሽ መሸፈን ነው? ገላን ያለመታጠብ ነው? አንገትን መድፋት ብቻ ነው? ቀስ ብሎ መናገር ነው? ኋላ ቀርነት ነው? አይመስለኝም፡፡ ቴሌቭዥን አለማየት፣ኢሜይል አለመጠቀም ነው? ከጸሎት መጻሕፍት በቀር ሌላ ነገር አለማንበብ ነው? መንፈሳዊነትኮ በመንፈስ ቅዱስ መመራት ነው፡፡ ራስን ማሸነፍ ነው፡፡ አእምሮን እና ልቡናን ቀና እና ሰላማዊ ማድረግ ነው፡፡ ለመሆኑ የውስጡ መንፈሳዊነት አይደለም እንዴ ወደላይ መገለጥ ያለበት፡፡ ስለ ሐዋርያት ስንናገርኮ የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ የሥጋቸው ቅድስና ለልብሳቸው፣ የልብሳቸው ቅድስና ደግሞ ለጥላቸው ተረፈ ነው የምንለው፡፡ መንፈሳዊነቱ ከውስጥ ወደ ውጭ እንጂ ከውጭ ወደ ውስጥ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ጊዜ «መንፈሳዊነት» ከ «መንፈሳይነት» ጋር እየተመሳሰለ የምንቸገር ይመስለኛል፡፡ ዲያቆን ኤፍሬም እሸቴ ነው ይህችን ቃል ያመጣት፡፡ ከሁለት ቃላት «መንፈሳዊ» እና «መሳይ» ከሚሉ ቃላት ቆራርጦ «መንፈሳይ» የሚል ቃል ፈጠረ፡፡ ትርጉሙም «መንፈሳዊ መሳይ» ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች መንፈሳውያን ይመስላሉ እንጂ አይደሉም፡፡
አባ ኤፍሬም ሶርያዊ ባስልዮስን ለማየት በሄደ ጊዜ ስለ ክብረ ወንጌል ሲል ከላዩ የወርቅ ልብስ ለብሶ ፣ የወርቅ ወንበር ዘርግቶ፣ የወርቅ ጫማ ተጫምቶ በጉባኤው ላይ ባየው ጊዜ «ደገኛ መምህር የተባለው ባስልዮስ ይኼ ነውን?» ብሎ ነበር፡፡ በኋላ ግን ተአምራቱን አይቶ አድንቆታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የውጭ ገጽታ ውስጥን ሊገልጥም ላይገልጥም ይችላልና፡፡ ልክ ነው ክርስቲያናዊ አነጋገር፣ አለባበስ፣ አረማመድ፣ ገጽታ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት መንፈሳዊነት ጅልነት፣ ከርፋፋነት፣ ኋላ ቀርነት ወይንም ደግሞ፣ ንጽሕናን አለመጠበቅ ማለት ግን አይደለም፡፡ በመንፈሳዊነታቸው የሚደነቁት የቤተ ክርስቲያን ከዋክብት እነ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ጎርጎርዮስ ዘእንዚናንዙ፣ባስልዮስ ዘቂሳርያ በዘመኑ በነበረው የግሪክ ፍልስፍና እና ዕውቀት የበለጸጉ ነገር ግን ዕውቀታቸውን እናሥልጣኔያቸውን በወንጌል የቃኙ ነበሩ፡፡
ብዙዎቻችን ከውስጥ ለሚመነጩ ትእግሥትን፣ ደግነትን፣ ታዛዥነትን፣ ትኅትናን፣ አርቆ ማሰብን፣ ኀዘኔታን፣ ፍቅርን፣ ትጋትን ለመሰሉ ነገሮች ትኩረት አንሰጥም፡፡ ከዚያ ይልቅ ተዋንያን ሊያደርጉት የሚችሉትን የውጭ ገጽታን ብቻ በማየት መመዘን እንመርጣለን። እውነተኛው መንፈሳዊነት ግን ከመንፈሳይነት መለየት አለበት፡፡ መንፈሳይ ሰዎች የራሳቸው መለያ ባሕርያት አሏቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከውስጣዊ መንፈሳዊነት ይልቅ ለውጫዊ ነገሮች ትልቅ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ማንነታቸውን ለመሸፈን ሲሉ ሕግ ከሚፈቅደው በላይ ለውጫዊ ገጽታ ይጨነቃሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ የፀጉር አያያዝ የራስዋ ባህል አላት፡፡ እነርሱ ግን ፀጉር መታጠብን ኃጢአት ያደርጉታል፡፡ ክርስቲያኖች የሚለብሱት ልብስ ራሳቸውን የማያጋልጥ እንዲሆን ትመክራለች፡፡ እነርሱ ግን ልብስ ሁሉ መሬት ካልጠረገ ይላሉ፡፡ ያደፈ በመልበስ፣ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ይመስል እጅግ ቀሰስ ብለው በመናገር፣ ሰው መሆናቸውን ረስተው ምንም ነገር እንደማይበሉ እና እንደማይጠጡ በማሳመን፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ በመልበስ፣ ሰንሰለት በመታጠቅ፣ ትልልቅ መቁጠርያ እጃቸው ላይ በመጠቅለል፡፡ ይበልጥ መንፈሳዊ ሆነው መታየት ይፈልጋሉ፡፡
ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው በዱርዬ እና በሴተኛ አዳሪዎች ዘንድ ያለውን ያህል ፈሪሃ እግዚአብሔር በአገልጋዮች ዘንድ የለም ይል ነበር፡፡
አንዳንዶች በአገልግሎት እየበረቱ ሲሄዱ ከመንፈሳዊነት ወደ መንፈሳይነት ስለሚለወጡ፡፡ጋሽ ግርማ ከበደ ከሚያስተምረው ነገር የማልረሳው ቃል አለ፡፡ «ሰው የሚጠላውን ኃጢአት ደጋግሞ ይሠራዋል» ይላል፡፡ ለምንድን ነው ደጋግሞ ይሠራዋል ያለው? እኔ እንደ ተረዳሁት መጀመርያውኑ ይህ ሰው ውስጡ ያላመነበትን እና ሊያደርገው የማይፈልገውን ነገር ነው ለማስመሰል ሲል እያወራ ያለው፡፡ ስለዚህም በውስጡ ያንን የጠላውን ነገር ላለማድረግ መንፈሳዊ ተጋድሎ ስለማያደርግ ደጋግሞ ሲሠራው ይገኛል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች መንፈሳያን ስለ አንድ
ሰው መንፈሳዊነት ደጋግመው በጥላቻ ወይንም በንቀት፣ ወይንም ደግሞ በመመጻደቅ የሚያወሩ ከሆነ ያንጊዜ አንዳች ነገር ተረዱ፡፡ ሳያስቡት እየተናገሩ ያሉት ስለ ራሳቸው ነው፡፡ መንፈሳውያን ሰዎች ስለሌሎች ውድቀት ሲያነሡ ከርኅራኄ እና ከኀዘኔታ ጋር ነው፡፡ የደስታ ስሜት አይሰማቸውም፡፡ እንደ ጀብዱም አይቆጥሩትም፡፡ ለዚህም ነው በቅዳሴ አትናቴዎስ ሊቁ ስለ አዳምና ሔዋን አንሥቶ «እኛስ እናንተን ልንወቅሳችሁ አንችልም» በማለት የተናገረው፡፡ መንፈሳውያን ይነበባሉ፤መንፈሳያን ግን ይታያሉ፡፡ መንፈሳውያን ይቀመሳሉ፣ መንፈሳያን ግን ይላሳሉ፡፡ መንፈሳውያን ያዳምጣሉ፤ መንፈሳያን ግን ይለፈልፋ፡፡ መንፈሳውያን ያስተውላሉ፤ መንፈሳያን ግን ይቸኩላሉ፤ መንፈሳውያን ያጠግባሉ፣
መንፈሳያን ግን ያቁለጨልጫሉ፡፡ መንፈሳውያን ይመዝናሉ፤ መንፈሳያን ግን ያፍሳሉ፡፡ መንፈሳውያን ያርማሉ፤ መንፈሳያን ግን ይተቻሉ፡፡ መንፈሳውያን ጠላቶቻቸውን አንድ ሺ ዕድል ይሰጣሉ፤ መንፈሳያን ግን ወዳጆቻቸውን ጠላቶቻቸው ለማድረግ አንድ ሺ በር ይከፍታሉ፡፡ መንፈሳውያን ይጾማሉ፣ መንፈሳያን ይራባሉ፤ መንፈሳውያን ይጸልያሉ፣ መንፈሳያን ግን ይናገራሉ/ያነባሉ፡፡ መንፈሳውያን ሱባኤ ይይዛሉ፣ መንፈሳያን ግን ስለ ሱባኤያቸው ያወራሉ፡፡ መንፈሳውያን ይሰጣሉ፣ መንፈሳያን ግን ሲሰጡ ያሳያሉ፡፡ መንፈሳውያን ቃለ እግዚአብሔርን ያስተምራሉ፣ መንፈሳያን ግን በራሳቸው ቃላት ይጠበባሉ፤ መንፈሳውያን ወደ ውስጥ፣ መንፈሳያን ወደ ውጭ ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን የነገን፣ መንፈሳያን የዛሬን ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን ምክንያቱን፣ መንፈሳያን ድርጊቱን ያያሉ፡፡ መንፈሳውያን ራሳቸውን፣ መንፈሳያን ሌላውን ያያሉ፡፡
መንፈሳውያን ከመፍረዳቸው በፊት ይመክራሉ፤ መንፈሳያን ከፈረዱ በኋላ ይመክራሉ፡፡ መንፈሳውያን ዘጠኝ ጊዜ ለክተው አንድ ጊዜ ይሰፋሉ፣ መንፈሳያን ግን ዘጠኝ ጊዜ ሰፍተው አንድ ጊዜ ይለካሉ፡፡ መንፈሳውያን ከመናገራቸው በፊት ያስባሉ፣ መንፈሳያን ከተናገሩ በኋላ ያስባሉ፡፡ መንፈሳውያን ይወስናሉ፣ መንፈሳያን አስተያየት ያበዛሉ፡፡ መንፈሳውያን ሰው እንዳይሞት በችግሩ ጊዜ ይረዳሉ፣ መንፈሳያን ግን ሰው ሲሞት የልቅሶ ትርኢት ያሳያሉ፡፡ መንፈሳውያን ስለ ሌሎች በጎ መናገርን ያዘወትራሉ፣ መንፈሳያን ስለ ራሳቸው በጎ መናገርን ይፈልጋሉ፡፡ መንፈሳያን ነጭ እና ጥቁር ብቻ ያያሉ፣ መንፈሳውያን ግን ግራጫንም ጨምረው ይመለከታሉ፡፡ መንፈሳዊ ሰው አንድ ሰው ነው፡፡ መንፈሳይ ሰው ግን ሁለት ሰው ነው፡፡ ውጩ ሌላ ውስጡ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ገና ያልተሸነፈ፣ እንዲያውም እየገነገነ እና እየገነተረ የሚሄድ ክፉ ጠባይ አለባቸው፡፡ አይጋደሉትም፡፡ አይጸየፉትም፡፡ ሊያሸንፉት አይፈልጉም፡፡ አይቃወሙትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ጥሩ ተዋናይ በአለባበስ፣ በአነጋገር፣ በአረማመድ፣ በመቅለስለስ፣ በመሸፋፈን እና ለሰው መስለው በመታየት ሊገልጡት የሚፈልጉት ሌላ ማንነት ደግሞ አላቸው፡፡ ይህ የውስጥ ማንነት አንድ ቀን ያሸንፍና እንደ ዴማስ ያስኮበልላቸዋል፡፡ ያን ጊዜ በሰው ይፈርዱ የነበሩትን ነገር ሁሉ አብዝተው ያደርጉታል። ወጣ ወጣ እና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ የተባለው ይደርስባቸዋል፡፡ አንዳንዴ መንፈሳይነት ሕይወት ሳይሆን በሽታ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ያውም የአእምሮ መዛባት/ mental disorder/፡፡ በሁለት ማንነቶች መካከል እየተምታቱ መኖር፡፡ መንፈሳዊ ሰው ኃጢአት ቢሠራ እንኳን ንስሐ ይገባበታል፡፡ ያርመዋል፡፡ ይጋደልበታል፡፡ ኃጢአቱን በመሸፈን እና በማስመሰል ሳይሆን በመጋደል እና በማስወገድ ያምናል፡፡ መንፈሳይ ሰው ግን ሌሎች እንዳያዩት እንጂ እግዚአብሔር እንዳያየው አይጨነቅም፡፡ አሁን እኛ እስኪ ራሳችንን እንየው መንፈሳዊ ነን ወይስ መንፈሳይ?

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.