Monday, May 25, 2020
Home > ዜና > ዶክመንተሪው ከሆነው የሰናፍጭ ቅንጣት ታክሏል እንኳን አልዳሰሰም፤

ዶክመንተሪው ከሆነው የሰናፍጭ ቅንጣት ታክሏል እንኳን አልዳሰሰም፤

ዶክመንተሪው ከሆነው የሰናፍጭ ቅንጣት ታክሏል እንኳን አልዳሰሰም፤ የሳይቤሪያ ጉድ፤ የ8 ቁጥር ገበና፤ የሸራተንና የጣውላ ቤት ስቆቃዎች፤ የነ አንዱዓለም፣ የነ ንግስቲ፣ የዋልድባ መነኮሳት፣ የሙስሊም ወንድሞቻችን፤ ዛሬም በገጠመው የወገብ ህመም ምግብ ቀንሶ የሚኖረው የተመስገን ደሳለኝ ስቃይ፤ ገና ምን ተነገረንና

ትናንት ምሽት በየቤቱ ሀዘን ነበር፤ በየቤቱ እንባ ፈሷል፡፡ እናቶች አምርረው ተንበርክከዋል፡፡ ወጣቶች አንገት ደፍተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆኑን የጠላውን ቤት ይቁጠረው፡፡ መሪር እና በጣም የሚያሳዝን ዘጋቢ ፊልም ነበር፡፡የተጋነነ የሚመስላቸው የዚያ ማዶ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አንሶ የተሰራ እንጂ ተጋኖ የተወራ የስቃይ ታሪክ አይደለም፡፡

ከወራት በፊት አማራ ብዙሃን ሰለባዎችን አቅርቦ ነበር፡፡ ጌታቸው ሽፈራሁ በስቆቃ ድምጾች ስቆቃውን ዘግቦልናል፡፡ አበበ ካሴ እንዴት እንዳደረጉት የምናውቀው ዘጋቢ ፊልሙ ሳይሰራ ነበር፡፡ኦነግ ተብሎ የተገደለውን አየለ በየነን ታሪክ ሚስቱ እያነባች ስታወራው አንብበን ነበር፡፡ የአርማዬ ዋቄ ወላጅ አባት ስለልጃቸው አሟሟት መች አወሩ? ሸዋንግዛው የሺጥላ ምን ተሰማለት? ማስረሻ ሰጤ ላይ የደረሰው ግፍና በደልስ? ይሄ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ አይደለም ይልቁንስ ዘር ማጥፋት ነው፡፡ሰው በኦሮሞነቱ ብቻ ተሰቃይቷል፡፡

አማራ መሆን አንገት ያስደፋበት የጨለማ ዘመን ነበር፡፡ ዘርዕያቆብ አዝመራው ከዳባት አዲስ አበባ መጥቶ የተሰቃየው በዘሩ ምክንያት ነው፡፡

እነ ሚፍታህ ሼህ ስሩር ያ ሁሉ በደል የደረሰባቸው ሙስሊም በመሆናቸው ነው፡፡ ኢስላማዊ አሸባሪነት አለ ብሎ የመንግስት ገንዘብ ለመዝረፍና በጀት ለማጋበስ የታቀደ የደህንነቱ ሴጣናዊ ስራ ሰለባ ሆነው ነው፡፡

ንግሥቲ ጥፍሮቿን በፌስታል ይዛ ቃሊቲ የወረደችው አማራ ነኝ በማለቷ ነው፡፡ ሚስባህ ከደር ኑሮው የተበተነው፣ የታሰረው የተሰቃየው ብሔሩ ከዶክተር ብርሃኑ ነጋ ብሔር ስለገጠመ ነው፡፡ እና ምኑ ተወራና ነው? ምኑ ተነገረና ነው? ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ እየራበው እስኪጠግብ የማይበላው ወገቡ ላይ በደረሰበት ጉዳት ሰውነቱ ስለማይሸከም የደረሰበት ስቆቃ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡

የዋልድባ መነኮሳት ለምን ተሰቃዩ? ቅዱሱ ስፍራ አይታረስም ብለው አይደለም? ለምን ተሰቃዮ? ለምን የምንኩስና ልብሳቸውን ለመግፈፍ ተፈለገ? እምነት ያለው የፈጠራቸው ሰዎች እንዲህ ማድረግስ ነበረባቸው?ይሄ ዘጋቢ ፊልም እንደ ቀድሞው አይመስለንም፡፡

አዲስ አበባ በ97 ምርጫ በሩህሩህ የጸጥታ ሃይሎች ጉንጯን ስትሳም እንዳልነበረች እንኳን እኛ ዓለም ያውቀዋል፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ህጻናት የሚገድል ስርዓት፣ እናቶችን የሚደፋ ፓርቲ ነበር፡፡ ያ ፓርቲ የሰራው ስራ ተጋኖ የቀረበ የመሰለው ሞኝ ነው፡፡ እውነት ነው ውሸት ነው የሚለው ለማወቅ እያንዳንዱ ቤተሰቡን ያንኳኳ ችግር ስለሆነ በየቤቱ መጠየቅ ከቤተሰቡ አባል ማወቅ ይችላል፡፡

የገራፊ ዳኞችን የዕለት ውሎ እንደዛሬው ብርሃን ሳይታይ ጌታቸው ሽፈራሁ በየቀኑ ፍርድ ቤት እየዋለ ይዘግብልን ነበር፡፡ ስም እንኳን እኛ ባልነው እንጂ እናንተ ባላችሁት አትጠሩም ብለው ሲያላግጡ የነበሩ ዳኞች፤ ወልቃይት የትግሬ ነው ብለው እየጻፉ ወልቃይት የአማራ ነው በሚሉ የማንነት ጠያቂዎች ላይ እንዲፈርዱ የተሰየሙ ዳኞች ገበና መች ተነገረ? ምኑ ተወርቶ ነው የተጋነነ የሚመስለው?

የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እንኳን የሆነው አልተወራም፡፡የሀሰት ምስክር ሁኑ ተብለው የተሰቃዩትስ? ጎንደርና ቂሊንጦ እንዲቃጠል ተደርጎ በጥይት የተቆሉትስ? ጨለማ ቤት የማቀቁትስ? የገቡበት ያልታወቁትስ? ጋሞ በመሆናቸው ብቻ የተሰቃዩት የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች፤ ጉራጌ በመሆናቸው ከሱቃቸውም ከሀገራቸውም የተፈናቀሉትስ? አማራ በመሆናቸው ያ ሁሉ ስቃይ የደረሰባቸውስ?

ኦሮሚኛ የታራሚ ቋንቋ እስኪሆን በኦነግ ስም የታጎሩትስ? ድምጻችን ይሰማ ብለው በመጠየቃቸው አሸባሪ ተብለው የተሰቃዮት ሙስሊሞችስ? ዋልድባን ለመታደግ መቀመቅ የገቡት አባቶችስ? ገና አልተወራም ገና አልተነገረም፡፡የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሄንን በደል የሚክሰው ሥርዓት ይፈልጋል፡፡ ሕገ መንግስቱ እንዲከበር ይጠይቃል፡፡ ወንጀለኛ በወንጀሉ እንዲጠየቅ መደረግ አለበት፡፡

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.