Monday, May 25, 2020
Home > ዜና > የአዴፓ ሹም-ሽረት የጉልቻ መለዋወጥ ነውን? – በመስከረም አበራ

የአዴፓ ሹም-ሽረት የጉልቻ መለዋወጥ ነውን? – በመስከረም አበራ

“በፈቃዳቸው ስልጣን አስረከቡ” የተባሉት አቶ #ገዱ ስልጣን ለመልቀቅ ያስገደዳቸው ድጋሜ የማንንም የበላይነት ተሸክሞ መኖር የማይሻበት የብስለት ደረጃ ላይ የደረሰው የአዴፓ ካድሬ ግፊት መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ኦህዴድ ወደ የበላይነት እና አምባገነንነት የሚደርገውን ጉዞ፣ የትግራይ ክልል የሚያደርገውን ድንፋታ እና የጦር ቱማታ ዝም ብሎ የሚያየው የአቶ ገዱ ዳተኛ አካሄድ ለአዴፓም ሆነ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አደገኛ ነገር ይዞ የሚመጣ ውጤት ይኖረዋል፡፡ ይህን አደገኛ አካሄድ ልጓም የሚያስይዝ አዲስ አመራር ማስፈለጉም ሳይሆን አይቀርም ዶ/ር አምባቸውን ወደ ስልጣን ያመጣቸው፡፡ ዶ/ር አምባቸው ለዚህ ብልሃት ያለው ፖለቲካዊ አካሄድ ትክክለኛው ሰው ናቸው አይደሉም? የሚለውን በእርግጠኝነት ለመናገር አሁን ጊዜው ባይሆንም አንዳንድ ነገሮችን ማንሳት ግን ይቻላል፡፡

የለማ/አብይ መንግስት ስልጣን በተረከበት ሰዓት ዶ/ር አምባቸው የንግድ እና እንዱስትሪ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ ግን ከዚህ ወንበር እንዲነሱ ሆኗል፡፡ ዶ/ር አምባቸው በተነሱበት ወንበር የተቀመጡት ደግሞ ተጋዳሊት ፈትለወርቅ ገ/እግዚብሄር (ሞንጆሪኖ) ናቸው፡፡ ሰው በሰው ሲተካ አንድም ተተኪው ከቀዳሚው ይሻላል ተብሎ፤ ሁለትም ለፓርቲያዊ የስልጣን ቅርምት ነው፡፡ ሞንጆሪኖ ከዶ/ር አምባቸው የተሻሉ ሰው ሆነው በወንበሩ ተቀምጠው ከሆነ ደግ ቢሆንም በኢህአዴግ ቤት ይህን መጠበቅ አስቸጋሪ ይመስለኛል፡፡

የሆነ ሆኖ ዶ/ር አምባቸው ከሚኒስትርነት ተነስተው ብዙም ፖለቲካዊ ጉልበት በሌለው የአማካሪነት ቦታ ላይ መቀመጣቸው በአዴፓ ካድሬዎች እና ደጋፊዎች ዘንድ ጉም ጉም ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህ ላይ ዶ/ር አምባቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርገው ሊሾሙ እንደሆነ ከተወራ በኋላ ቀረ፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ብአዴኗን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ከምክትል ከንቲባነት ተነስተው እምብዛም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማምጣት በማያስችለው የትራንስፖርት ሚኒስትርነት ቦታ ላይ ተመደቡ፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ሲያያዝ ኦዴፓ መራሹ መንግስት ሆን ብሎ የአዴፓ ጠንካራ ሰዎችን ከመሃል እያሸሸ እንደሆነ በአዴፓ ካድሬዎች ዘንድ ቁጭት የጨመረ መረዳትን አመጣ፡፡

ይህን ሁሉ አዲስ አበባ ተቀምጠው የሚያጤኑት ዶ/ር አምባቸው የዶ/ር አብይን ኦዴፓ የበላይነት ጉዞ መረዳታቸው አይቀርም፡፡ እንደ ግለሰብም ከስልጣን ማዕድ መገፋታቸው ጥሩ ስሜት የለውም፡፡ በዚህ ላይ በኢህአዴግ ቤት ስልጣን ዋና ነገር ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ዶ/ር አምባቸው ከአቶ ገዱ በጣም በተለየ ሁኔታ የአማራ ክልል ህዝብ የተጋረጠበት አደጋም ሆነ ኦዴፓ የገባበት አጣብቂኝ የሚሰማቸው ሰው እንደሆኑ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ፤ በአደባባይ የሚያደርጓቸው ንግግሮችም ምልክት ናቸው፡፡

ይህ የዶ/ር አምባቸው ቁጭት በተለይ የአማራ ክልል ከትግራይ ክልል ጋር ለገባው ፍጥጫ ችኩል ውሳኔ እንዳያስወስናቸው ሰፊ ስጋት አለ፡፡ ይህን ስጋት ዶ/ር አብይም እንደሚጋሩት በትናንቱ የባህርዳር ንግግራቸው “ዶ/ር አምባቸው ወደ መቀሌም ወደ አምቦም ጎራ በል” በሚል አይነት ንግግራቸው ጠቆም አድርገዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ዶ/ር አምባቸው የአቶ ገዱን ያህል ለአብይ/ለማ መራሹ መንግስት የሚመቹ አይመስልም፡፡ የዶ/ር አምባቸው ሹመት ዶ/ር አብይ ቀድመው የማያውቁት እና ድንጋጤን ጭምር የፈጠረባቸው የሚመስል ነገር ከሁኔታቸው ይነበብ ነበር፡፡ ከዚህ የምንረዳው ኦዴፓ እና አዴፓ እየተነጋገሩ መስራታቸው እንደ ቀድሞው እንዳልሆነ ነው፡፡ በርግጥ ተደጋግፎ መስራቱን ቀድሞ ጥያቄ ውስጥ የከተተው ማን እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ቢያስቸግርም አዲስ አበባ የኦሮሚያ ንብረት እንደሆነች የለፈፈው ኦዴፓ ነገሩን እንዳበላሸ መገመት ይቻላል፡፡

****

ፀሃፊ፦ Meskerem Abera

(ሙሉ ፅሁፉን ለማንበብ ከታች ያለውን ሊንክ/ምስል ይጫኑ)

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.