Friday, November 15, 2019
Home > ማህበራዊ > በኢትዮጵያ 2012 ዓ.ም የ9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት

በኢትዮጵያ 2012 ዓ.ም የ9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት

በ2012 ዓ.ም የ9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ መታቀዱ ተገለጸ

************************************

በ2012 ዓ.ም የ9 በመቶ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ መታቀዱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የ2012 ዓ.ም ረቂቅ በጀት የፊስካልና ማክሮ ኢኮኖሚን መሰረት በማድረግ መዘጋጀቱን ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ በጀቱ በዛሬው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የ2012 በጀት ብር 387 ቢሊዮን ብር ሆኖ መመደቡንና ይህንኑ በዋናነት ከታክስና ከሌሎች ዘርፎች ለመሰብሰብ መታቀዱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

የ2011 ዓ.ም የታክስ አሰባሰብን መሰረት በማድረግ በ2012 ዓ.ም የተሻለ የታክስ አፈፃፀም እንዲኖር ታቅዷል ብለዋል፡፡

በ2011 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው የ11 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ቢጠበቅም በተደረገው ግምገማ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡

ለ2012 ዓ.ም ከተመደበው በጀት ውስጥ 63 በመቶ የሚሆነው ለትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና እና ለመሳሰሉ የተመረጡ ዘርፎች መመደቡን ገልጸዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት 346.9 ቢሊዮን ብር ነበር።

ባለፈው ሰኔ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የምኒስትሮች ምክር ቤት የ2012 ዓ.ም. ረቂቅ በጀትን አፅድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲልክ ለመደበኛ ወጪዎች 109 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ቢሊዮን ብር፤ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 140 ቢሊዮን ብር፤ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 6 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተገልጿል።

የሀገሪቱን የባለፉት 3 ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተም ኢኮኖሚው የተለያዩ ተግዳሮቶች ያጋጠሙት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ የሀገሪቱን የበጀት ጉድለት ከውጭና ከውስጥ ብድር ለመሸፈን መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡና በቁጠባ እንዲጠቀሙ ለማድረግ የተሰራው ስራ ጅምር ውጤት አሳይቷል ብለዋል አቶ አህመድ፡፡

የመንግስት ፕሮጀክቶች በታቀደው ጊዜ እንዲፈፀሙ ከፍተኛ ክትትል እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ባጠቃላይ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች በጀቱን ለተመደበላቸው ዓላማ በማዋል የተሳካ አፈፃፀም እንዲያስመዘግቡ አሳስበዋል፡፡

በተለይም የተመደበው በጀት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ርብርብ እንዲያደርግም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዮሴፍ ለገሰ

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.