Monday, May 25, 2020
Home > ማህበራዊ > የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሚና

የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ሚና

ሜ/ጄ መሐመድ ተሰማ የሚባል የመከላከያ ሰራዊት ኃላፊ በሰጠው መግለጫ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን መከላከያ ሰራዊቱን ከሕዝብ ጋር በማጋጨት አንደኛ ተጠያቂ ነው ብሎ ሲከስሰው ሰማሁ።

***********************************

ባለፈው ሳምንት ግለሰቦችንና ሚዲያዎችን በሕግ እንጠይቃለን ሲሉ መጀመርያ ያሰብኩት ተመስገን ደሳለኝን ነው። ተመስገን ደሳለኝ የተባለውን ወንጀል ስለሰራ አይደለም። በመረጃ አስደግፎ የተቀሙን ብልሹነት ለሕዝብ ስላጋለጠ እንጅ።

የመከላከያ ኃላፊው ተመስገንን በወንጀል ተጠያቂ ነው ብሎ አላለፈውም። በተቋም ስም መግለጫ እየሰጠ እንደ አልፎ ሂያጅ ነገረኛ ዘልፎታል።

ተመስገን ደሳለኝን ተራ አለመሆኑን የሚያውቅ የሚያውቀው ሆኖ “ተራ፣ ለኢትዮጵያ ምንም ያላደረገ፣ በኮምሽን የሚፅፍ……” እያለ ሊያሸማቅቅ ሞክሯል። መግለጫውን የሰጠው የመከላከያ ኃላፊ በሰሜት ዘለፋ ውስጥ የገባው ዝም ብሎ አይመስለኝም።

ተመስገን ደሳለኝ በእጅጉ አበሳጭቷቸዋል። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተራ ሳይሆን መከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ ያሉ አመራሮች “ተራ” ብለው የተውትን መረጃ የማይንቅና እነዚህን መረጃዎች ገጣጥሞ ጥፋታቸውን ማመን በሚያቅታቸው አኳኋን ሕዝብ ፊት ስለሚዘረግፍባቸው ነው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የመከላከያ ሰራዊቱን ጉዳይ በመተንተን የተመስገን ደሳለኝን ያህል ብቁ ሰው ስለመኖሩ አላውቅም።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ካለው ጥልቅ መረጃ የተነሳ መግለጫ የሚሰጡት የመከላከያ ሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የረሷቸውን እዞች፣ መኮንኖች……ሁሉ ሊያስታውሳቸው ይችላል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን የሚስጥር ጉራንጉር በደንብ የተረዳው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተቋሙ ውስጥ ሕዝብ አያውቀውም ተብሎ የታጨቀን ጉዳይ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ በርትቶ ሲሰራ ቆይቷል።

ይህ ስራው ለተቋምና ሀገር ግንባታ ትልቅ ድርሻ ቢኖረውም ማለባበስ የሚፈልጉት ኃይሎች አልወደዱትም። እሳት ጎርሰው የስድብ ናዳ አውርደውበታል። የተመስገንን መረጃዎች የሚያነብ ሰው ብዙ ቁም ነገሮችን ያገኛል።

የመከላከያ ሰራዊቱ በተመስገን ደሳለኝ ላይ የሰጠውን አሳፋሪና ከተቋም የማይጠበቅ መግለጫ የተመለከተ ደግሞ ተመስገንን ይበልጡን ያደንቀዋል።

እነ መሃመድ ተሰማ “ተራ” ብለው ለማጣጣል የደከሙበት ተመስገን ደሳለኝ የእነሱን ፕሮግራሞች እንኳ ንቆ አይተውም። መረጃን ተራ ብሎ አያልፍም። ከእነሱ ፕሮግራሞች የተለቃቀሙትን “ተራ” የሚመስሉ መረጃዎች ገጣጥሞ ተራራ የሆነውን ችግራቸውን ሲያጋልጥባቸው ይህን ብቃቱን “ተራ” በሚል የብስጭት መግለጫቸው የሚያራክሱ መስሏቸዋል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዚህ ሀገር “ለውጥ” ትልቅ ድርሻ ከተጫወቱት ግለሰቦች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። በአሁኑ ወቅት “የለውጥ ኃይል ነው” የሚባሉት አዴፓና ኦዴፓ ከትህነግ/ሕወሓት አሳዳሪነት እንዲላቀቁ የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ያህል የተጋ ስለመኖሩ እንጃ! ገዥዎቹ ውለታ ስለማያውቁ እንጅ ትህነግን ገመናዋን በማጋለጥም ሆነ የለውጥ ኃይል የሚባለውን ገና ድሮ ጀምሮ በመምከር ላደረገው ሚና ሽልማት የሚገባው፣ ክብር የሚቸረው ተመስገን ደሳለኝ ነበር። ለ”ለውጡ” ትልቅ ድርሻ ኖሯቸው ካልተመሰገኑት መካከል አንዱ ዋነኛው ተመስገን ደሳለኝ ነው።

ሆኖም ለበጎ አስተዋፅኦው ያልተመሰገነው ተመስገን ደሳለኝ በሀቀኛ መንገዱ ሲቀጥል ገዥዎቹ በተቋም ደረጃ ዘለፋ እየፈፀሙበት ነው።

ሀቅ በመናገሩ ወደፊት ምን ሊገጥመው እንደሚችል በደም ፍላት እየነገሩን ነው። የተረኛ ገዥዎችን አሳፋሪ ተግባር በማጋለጡ በአደባባይ፣ ትህነግ/ሕወሓት እንኳ አድርጎት በማያውቀው ሁኔታ በአደባባይ እየዘለፉ መግለጫ ሰጥተውበታል።

ተመስገን አያደርገውም ይሆናል እንጅ (ቢያደርገው ይመረጣል) የመከላከያ ሰራዊቱ አመራር በሚዲያ ወጥቶ በተመስገን ላይ የፈፀመው ዘለፋና ስም ማጥፋት በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው። ምንም እንኳ ሕጉ የባለ መሳርያዎች ቢሆንም በብዕሩ እንዳንቀጠቀጣቸው ሁሉ ፍርድ ቤት አቅርቦ እነሱንም ፍርድ ቤቱንም ቢታዘበው መልካም ነው!

እንዲመዘገብ የሚገለው!

የዘመኑ ገዥዎችም በቀዳሚነት ጥርስ ውስጥ ካስገቧቸው ጋዜጠኞች ተመስገን ደሳለኝ አንደኛው ነው። በየሳምንቱ የምትወጣው ፍትሕ ጋዜጣና የእነ ተመስገን ትንታኔ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚፈጥሩት በላይ በገዥዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ነው።

እነ ተመስገን የመንግስትን የሚስጥር ጓዳ በርብረው ለሕዝብ የሚያደርሱት መረጃና ትንታኔ ገዥዎችን እርቃን የሚያስቀር ነው። ይህን ገዥዎቹ ያውቁታል።

በዚህም ምክንያት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ገዥዎቹ ጥርስ ውስጥ ከገቡት ሰዎች መካከል ቀዳሚው ሆኗል። እኔ በበኩሌ ገዥ የሰኔ 15 ክስተትን ተከትሎ ገዥዎቹ ጉዳት ሊያደርሱባቸው ይችላሉ ብዬ ካሰብኳቸው ሰዎች ተመስገን አንደኛው ነው።

እንደ ታናሽ ወንድም ስጋቴንም አጋርቸዋለሁ። በሚዲያ እሳት ጎርሰው ዘለፋ የሚፈፅሙት አመራሮች በተመገን ላይ ጉዳት አያደርሱም ለማለትም አይቻልም።

እነሱ እንዲህ በንዴት ሲዘልፉት ያየ ሌላ አካልም ጉዳት ቢያደርስ ተጠያቂ መሆን ያለበት ራሱ መከላከያ ሰራዊቱና መንግስት ነው። የመከላከያ ሰራዊቱ አመራር በዛቻና ዘለፋ የሰጠው መግለጫ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ለሚደረጉ ማንኛቸውም ነገሮች ገፊ ሆኖ መመዝገብ ይገባዋል!

ጌታቸው ሽፈራው

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.