Monday, May 25, 2020
Home > ማህበራዊ > በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የወላይታ ብሔር አባላት የተሰጠ መግለጫ

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የወላይታ ብሔር አባላት የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የወላይታ ብሔር አባላት የተሰጠ መግለጫ

ዋሽንግተን ዲሲ

***********************************

በአሁኑ ወቅት ደቡብ ክልልን እየመራ የሚገኘው ደኢህዴን ከክልሉ ህዝቦች የተነሱትን የአደረጃጀት ጥያቄ ለመመለስ ውይይት ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል።

ድርጅቱ ስምንተኛ (8) ቀን በያዘው ስብሰባ ግልጽ ለሆኑ ህዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እየከበደው መሆኑ እያስተዋልን እንገኛለን።

ህዝብ ላነሳቸው ህጋዊ ጥያቄዎች በህገመንግስቱ አግባብ በቀላሉ መልስ መስጠት እየተቻለ ሂደቱን ለማወሳሰብ መምረጡ የድርጅቱን የቆየ ፀረ-ህዝብ ባህልን ግልጽ አድርጎ ያሳየ ሂደት ነው ብለን እንወስዳለን።

የወላይታ ህዝብ የተለያዩ ህጋዊ መንገዶች በመጠቀም በክልልነት ለመደራጀት ግልጽ የሆነ መልዕክት ለመንግሥት ካስተላለፈ ሰንበትበት ብሏል።

ነገርግን ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እስከአሁን አልተሰጡም።

በመሆኑም ድርጅቱ የህዝብን ፍላጎት ወደ ጎን ባደረገ መንገድ የሚወሰን ማነኛውም አይነት ውሳኔ የክልሉን ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥል፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያበላሽና ለአገር አንድነት የማይጠቅም መሆኑን ተገንዝቦ ለህዝቦች ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ እናሳስባለን።

አገርቷ የምትከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት በይበልጥ ማጎልበት የሚቻለው በደቡብ አከባቢ ለተነሱ ማዋቅራዊ ጥያቄዎች የህዝብን ፍላጎት ባማከለ መንገድ መልስ ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ እናምናለን።

አዲስቷ አትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃና ጠንክራ መቀጠል የምትችለው ፌደራላዊ ሥርዓቱን አጠናክራ ህብረብሔራዊ ሆና መቀጠል ስትችል ነው።

ህብረብሔራዊ ኢትዮጵያ ማረጋገጥ ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ በአገርቷ ደቡብ ክልል ላሉ ማንነቶች እውቅና ከመስጠት ባለፈ የህዝቦችን ክልል የመሆን ፍላጎት ማክበር ሲቻል እንደሆነ አበክረን እናምናለን። በዚህም መሠረት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የብሔሩ አባላት የሚከተለውን የአቋም መግለጫ ለማውጣት ተገደናል፦

በህገመንግስቱ የተደነገጉ መብቶች በአገርቱ ያሉ ብሔሮችን ሳይለይ ለሁሉም እኩል መሠራት ይጠበቅበታል። በዚህም መሠረት በህገመንግስቱ አንቀጽ 47 መሠረት የወላይታ ህዝብ ክልል የመሆን መብት በቀረበው የህዝብ ፍላጎት መሠረት መንግስት እንዲያከብረው ጥሪ እናቀርባለን።

የወላይታይ ህዝብ የሚያገል ማነኛውንም ውሳኔ በጽኑ እንቃወማለን፣ ደኢህዴን ከያዘው አጥፊ መንገድ ታርሞ የወላይታ ህዝብን የክልልነት መብት እንዲያከብር እናሳስባለን። በዚህ ስብሰባ የሚወሰን ማነኛውም አይነት ህዝብን የማያከብር ውሳኔ አጥብቀን እንቃወማለን።

የወላይታ ህዝብን የሚያገል ማነኛውንም ውሳኔ ለመታገልና ለመቀልበስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀን መሆናችንን እንገልጻለን።

እስከዛሬ ከወላይታ ዞን ምክርቤት ለክልሉ የገባው ክልል የመሆን ጥያቄ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለመላኩ ብሔሩን ለማጥቃት የተደረገ ሴራ አድርገን እንወስዳለን። ስለዚህ ከዚህ ጀረባ ያሉ ሀይሎች ለህግ ተገዢ ሆነው ለህዝቡ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ሰላም የሚረጋገጠው አገርቷ ህብረብሔራዊነቷን አስጠብቃ አሁን ያለውን የፌደራል ሥርዐቱን አስፍታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ ስታነጽ ነው።

ስለዚህ የወላይታ ህዝብ ክልል መሆን የፌደራል ሥርዓቱን የሚያጠነክርና የአገር አንድነትን አስተማማኝ መሠረት ላይ እንደሚያቆም ግንዛቤ ተወስዶ ቀና ምላሽ እንዲያገኝ ሁሉንም አይነት የሰላም ትግል እንደምናደርግ እንገልጻለን።

በደቡብ ክልል ያለው ሰላም የሚረጋገጠው የወላይታም ሆነ የሌሎች ህዝቦች ክልል የመሆን መብት ሲከበር በመሆኑ ይህ እንዲፈጸም ኢትዮጵያው ውስጥ ከሚገኙ ለክልሉ ህዝብ ቀናኢ አመለካከት ካላቸው የፌደራል ሀይሎች ጋር እንሰራለን።

በደቡብ ካሉ ህዝቦች ጋር ለጋራ ግብ አብረን የምንሰራ ሲሆን በክልሉ ህዝቦች የተነሱ ክልል የመሆን ፍላጎቶች እንዲከበሩ እንጠይቃለን።

ከዚህ ውጭ የህዝቦችን ፍላጎት በሃይል ለመጨፍለቅ የሚደረግ ማነኛውንም አይነት ሙከራን አጥብቀን እናወግዛለን።

ዋሽንግተን ዲሲ

ሐምሌ 5 2011 ዓ.ም

Leave a Reply

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.